የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል ማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል ማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል ማክበር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ገለጹ።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር እያደረገ ያለው ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑንም ተገልጿ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለማክበር በተደረጉ ዝግጅቶችና እና ራዝ ገዝ ለመሆን በተጀመሩ ሂደቶች ላይ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከታህሳስ 1943 ዓም ጀምሮ በሰው ሃይል ልማት፣ በጥናትና ምርምር ዙሪያ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ነው፡፡
እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ለማስተናገድና፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉ ህክምና ፈላጊዎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም መፍጠሩንም አብራርተዋል፡፡
የኢዩቤልዩ በዓሉ የሚከበረው ዩኒቨርሲቲው ያበረከተውን አስተዋጽኦ በመዘከር በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎችን ለማጠናከር በማለም ነው ብለዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ዩኒቨርሲቲው ያበረከተውን አስተዋጽኦ በመጽሐፍ ሰንዶ ይፋ የማድረግ፣ ዘጋቢ ፊልም፣ የአካዳሚክ ሴሚናሮች፣ የፓናል ውይይቶች፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የበጎ ፈቃድ ሳምንት መርኃ ግብሮች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን የሚያደርገው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚያግዘውንና ከ2024 እስከ 2028 ለአምስት ዓመት የሚመራበትን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን ሴኔት ህግ ከራስ ገዝ አዋጅና ከማቋቋሚያ ደንቡ ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል፡፡
ዓለም አቀፋዊነትና አጋርነት ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ ሃብት ማፈላለግ እና ምንጭ ማስፊያ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ የተማሪዎች ቅበላ እንዲሁም የምርምርና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ጸድቀው ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡