ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከብን ነው - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከብን ነው - አርሶ አደሮች
አምቦ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፡- ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከቡ መሆኑን የምዕራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
አርሶ አደሮቹ ከዚህ ቀደም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በተተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመው ዘንድሮም በችግኝ እንክብካቤው ላይ አተኩረዋል።
ከጨሊያ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አስፋው ድንቁ ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተራቆተ እና የተጎዳ ማሳቸው አገግሞ አሁን ላይ በፊት ከሚያገኙት ምርት በእጥፍ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የእርሻ ማሳቸው በጎርፍ ተጠርጎ ምርታማነቱ በመቀነሱ ስጋት ውስጥ ገብተው እንደነበረም አስታውሰዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በተከታታይ በተተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸር በመቀነሱ የእርሻ ማሳቸው ምርታማነቱ መጨመሩን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የጥራጥሬ ሰብሎችን እያለሙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው የተተከሉ ችግኞች የመሬቱን ለምነት የሚጠብቁ በመሆኑ ለከብቶቻቸው መኖ ማግኘታቸውንና አካባቢያቸውም መልካም ገጽፅታ መላበሱን አውስተዋል።
ሌላው አርሶ አደር ፋይሳ ቀነኒ በበኩላቸው፣ በአካባቢያቸው የተጎዳ መሬት በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት እንዲያገግም በመደረጉ ከዚህ ቀደም ከሚያለሙት የጥራጥሬ ሰብሎች በተጨማሪ ጥምር ጥቅም የሚሰጡ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡
መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ስለማይዘንብ ብዙ መቸገራቸውን አስታውሰው አሁን ላይ ግን ዝናቡም ወቅቱን ጠብቆ በመዝነቡ ምርታማነታቸው ጨምሮ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ በማስተባበር የእርከን ስራ ላይ የአፈር ለምነት እንዲጠብቅና የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ለተከታታይ ዓመታት በሰሩት ስራ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል።
የጨሊያ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርናና መሬት አስተዳዳር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢነዑ ተሾመ በበኩላቸው፤ በወረዳው በሚከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ስራ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡
በወረዳው በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለተተከሉት ችግኞች አስፈላጊው እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ከተጀመረ ወዲህ የአካባቢው ስነ ምህዳር ከመቀየሩም በላይ የአርሶ አደሮቹ ምርትና ምርታማነት መጨመሩን አመልክተዋል።
በወረዳው በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት መርሃ ግብር ከሃገር በቀል የዛፍ ችግኞች በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ ማንጐ፣ ሙዝ፣ አቮካዶ እና ቡና ጭምር መተከላቸውን ተናግረዋል፡፡