በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ129 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማ የአኩሪ አተር ሰብል ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ129 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማ የአኩሪ አተር ሰብል ተሰብስቧል
ገንዳውኃ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ129 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማ የአኩሪ አተር ሰብል ከብክነት በፀዳ መንገድ መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መመሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ተወካይ ቡድን መሪ ቻላቸው አቸነፍ ለኢዜአ እንደገለጹት የአኩሪ አተር ሰብል ከሌሎች ሰብሎች በላቀ ምርታማ በመሆኑ በአርሶ አደሮች እና በባለሃብቶች በሰፊው እየለማ ይገኛል።
በዚህም በምርት ዘመኑ በአኩሪ አተር ከለማው 148ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን በተደረገው ጥረት ከ129 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የደረሰውን ምርት ከብክነት በጸዳ መልኩ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የአኩሪ አተር ምርት ለወጪ ንግድና ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ግብዓት በማዋል የአገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እየሆነ በመምጣቱ ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
በዚህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባለው ሰብል ልማት ላይም ከ48ሺህ በላይ አርሶ አደሮችንና 526 ባለሃብቶችን በማሳተፍ ማልማት መቻሉን አውስተዋል።
በምርት ዘመኑ በአኩሪ አተር ከለማው ሰብል ከ4 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አርሶ አደር ጌታሁን እሸቱ እንዳሉት በአኩሪ አተር ከሸፈኑትን ሶስት ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ሁለት ሄክታር የሚሆነውን መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።
ዘንድሮ ካለሙት አኩሪ አተር ሰብል እስከ 70 ኩንታል እንደሚጠብቁ ጠቁመው የአኩሪ አተር መፈልፈያ ማሽን እንዲቀርብላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።
በዞኑ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሃብት ተወካይ የሆኑት ፋሲካው አብራራው በበኩላቸው 140 ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል።
በየቀኑ ከ80 በላይ የጉልበት ሰራተኞችን በመቅጠር እስካሁን ከ130 ሄክታር በላይ የሚሆነውን ምርት መሰብሰቡን ጠቁመው ከዚህም ከሁለት ሺህ 800 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያገኙ አስረድተዋል።
የአኩሪ አተር ሰብል ከደረሰ በማሳው ላይ የሚፈስ በመሆኑ በተዘራበት የጊዜ ቅደም ተከተል በወቅቱ በመሰብሰብ ከብክነት የፀዳ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዞኑ ባለፈው የምርት ዘመን 140ሺህ 700 ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ለምቶ ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።