ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍና ቀጣይነት ያለው የምግብ ለዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት የሚደገፍ 2ኛ ምዕራፍ የኩታ-ገጠም እርሻ ፕሮግራም ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ግብርናውን በማዘመን ሁሉን አቀፍና ቀጣይነት ያለው የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት ይደግፋል የተባለው 2ኛው ምዕራፍ የኩታ-ገጠም እርሻ ፕሮግራም ይፋ ሆኗል።

በመርሃግብር ላይ የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴን (ዶ/ር) ጨምሮ የዘርፉ ተዋንያን፣ አምባሳደሮች፣ የአጋር ድርጅቶች ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአየር ንብረት ጥበቃን መሠረት ላደረገ ግብርና ቅድሚያ በመስጠት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

ፕሮግራም ግብርናን የሚያዘምን የአርሶ አደሩን ህይወት የሚያሻሽሉ የተቀናጀ የግብርና ተግባራት የሚከናወኑበት መሆኑንም አንስተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጥረት የሚደግፍ ነው ብለዋል።

ፕሮግራሙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ህይወት ከማሻሻል ባለፈ ለሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ሚናው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።

ለፕሮግራሙ ውጤታማነት አጋር ድርጅቶችና የተለያዩ ተቋማት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ ዘጠኝ ስትራቴጂክ የግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአነስተኛ ማሳ አርሶ አደሮችን በፋይናንስና በቴክኒክ በመደገፍ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምርና የገበያ ትስስር የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ የኩታ ገጠም እርሻ ፕሮግራም በቡና በጥራጥሬና ቅመማ ቅመምና ቅባት እህሎች የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩና እሴት እንዲጨምሩ ያግዛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም