ኢትዮጵያ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታዋን ዛሬ ከደቡብ ሱዳን ጋር ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታዋን ዛሬ ከደቡብ ሱዳን ጋር ታደርጋለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
በዕለቱ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ከቀኑ 7 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ትጫወታለች።
በምድብ አንድ የምትገኘው ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ሩዋንዳን ዳዊት ካሳ እና ሁዜፋ ሻፊ ግቦች 2 ለ 0 አሸንፋለች። ምድቡንም በሶስት ነጥብ እየመራ ይገኛል።
በአሜሪካዊው ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው ታዳጊ ብሄራዊ ቡድኑ በጨዋታው ላይ ያሳየው ብቃት በብዙዎች አድናቆት አስችሮታል።
ተጋጣሚዋ ደቡብ ሱዳን ከሶማሊያ ጋር ባደረገችው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ሁለት አቻ መለያየቷ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈች ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ እድሏን ታሰፋለች።
በምድብ አንድ ሌላኛው መርሃ ግብር ሶማሊያ ከኬንያ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሶማሊያ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ከደቡብ ሱዳን ጋር ሁለት አቻ ተለያይታለች። ኬንያ በምድቧ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
በምድብ ሁለት መርሃ ግብር ሱዳን ከዩጋንዳ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ሱዳን በመጀመሪያ ጨዋታዋ በታንዛንያ 6 ለ 0 ስትሸነፍ በአንጻሩ ዩጋንዳ ብሩንዲን 4 ለ 0 አሸንፋለች።
በዚሁ ምድብ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ ታንዛንያ ከጅቡቲ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ታንዛንያ ሱዳንን 6 ለ 0 በመርታት የሴካፋ ማጣሪያን በድል ጀምራለች። ጅቡቲ በምድቧ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
በሴካፋ ዞን ማጣሪያ 10 ሀገራት በሁለት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። ማጣሪያው እስከ ህዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
በማጣሪያው ለፍጻሜ የሚያልፉት ሁለት ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።
እ.አ.አ በ2026 በሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ሞሮኮን ጨምሮ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።