ቀጥታ፡

በከተማው እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የአፋር ህዝብን እሴት በሚገልፅ መልኩ መከናወኑን ተመልክተናል - የከተሞች ፎረም ተሳታፊዎች

ሰመራ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ በሠመራ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የአፋር ህዝብን እሴት በሚገልፅ መልኩ መከናወኑን ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የከተሞች ፎረም ተሳታፊዎች ተናገሩ።

10ኛው የከተሞች ፎረም "የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት" በሚል መሪ ሐሳብ በአፋር ክልል ሠመራ ሎጊያ ከተማ በመከበር ላይ ይገኛል።

የሰመራ ከተማ ኮሪደር ልማትን የተመለከቱ የፎረሙ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት የአፋርን ባህልና አሴት የሚገልፅ የኮሪደር ልማት በሰመራ እየተገነባ ነው።


 

ከተሳታፊዎቹ መካከል ከወላይታ ዞን የመጣው በረከት አያኖ የሠመራ ከተማ ኮሪደር ልማት ሥነ ምህዳሩን ከግምት ያስገባና የህዝቡን እሴት በሚገልጽ መልኩ መገንባቱ ለእግር ጉዞም ሆነ ለተዝናኖት የተመቸ ነው ብሏል።

በሌላም በኩል የህብረተሰቡ እንግዳ ተቀባይነትና መስተንግዶ ሠመራን ውብና አስደሳች ከተማ እንዳደረጋትም ገልጿል።


 

ከከምባታ ዞን የመጣችው ወይንሸት ታዲዮስ በበኩሏ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገፅታ በሚመጥን መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብላለች።

የልማት ስራው የአፋር ህዝብን ባህልና እሴት በሚገልፅ መልኩ መከናወኑ ጉልህና የተለየ እንዳደረገውም ተናግራለች።


 

ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን የመጣው ዱርሳ አብዱልመሊክ በበኩሉ በሰመራ ከተማ እየተሰሩ ያሉ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች

ማራኪና ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚችሉ ናቸው ሲል ተናግሯል።


 

ሌላኛው ተሳታፊ ከምዕራብ አርሲ ዞን የመጣው ሞያታ ወልዴ እንደተናገረው በሰመራ ከተማ እየተከናወነ ያለው ኮሪደር ልማት የከተሞችን የመልማት አቅም ያሳየ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም