ቀጥታ፡

በአምራች ኢንዱስትሪ የተፈጠረው ከፍተኛ መነቃቃት ለዜጎች ሥራ ዕድል ፈጠራ ገንቢ ሚና እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ በአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የተፈጠረው ከፍተኛ መነቃቃት ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን የጉራጌ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ አስታወቀ።

20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጣ የጋዜጠኞች ቡድን የጉራጌ ዞን የልማት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝቷል።

የጋዜጠኞች ቡድን በጉራጌ ዞን በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።

የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ ሙራድ ያሲን፤ በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ለወጣቶች የሥራ ዕድል ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በጉራጌ ዞን በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማሩ 274 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የምርታማነት አቅም በማሳደግ ዘርፉን የበለጠ ለማስፋት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

አምራች ኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዞችም በየዓመቱ ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢንተርፕራይዞችን የምርታማነት አቅም ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት 21 ሞዴል ኢንተርፕራይዝ መፍጠር ማስቻሉን ተናግረዋል።

በሌማት ትሩፋት የወተት ልማት የተደራጁ ኢንተርፕራይዞችም የማህበረሰቡን የወተትና ወተት ተዋጽኦ ምርቶች አቅርቦት ፍላጎት በማሟላት በተመጣጣኝ ዋጋ እያስገኘ መሆኑን አብራርተዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ቀን ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ ህዳር 29 ቀን 2018 ዓም ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም