ሰውና ተፈጥሮ የተዋደዱበት ቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን - ኢዜአ አማርኛ
ሰውና ተፈጥሮ የተዋደዱበት ቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን
ሰውና ተፈጥሮ የተዋደዱበት ቆጠር ገድራ በጉራጌ ዞን ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ ነው።
ጥብቅ ደኑ ከጉራጌ ዞን ከወልቂጤ ከተማ በ42 ኪሎ ሜትር ርቀት በስተምሥራቅ በእዣ ወረዳ ቆጠር ገድራ ቀበሌ ይገኛል።
ጥብቅ ደኑ በበርካታ ሀገር በቀል ዛፎች የተሸፈነ፣ ሰውና ተፈጥሮ የተዋደዱበት፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ የህይወት እስትንፋስ ነው።
የቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን ቀልብን የሚስብ፣ ነፍስ በሀሴት የምትሞላበት፣ መንፈስ የሚታደስበት ውብ ስፍራ ነው።
ቆጠር ገድራ ተዳፋታማ በሆነ ስፍራ የሚገኝ ሲሆን ብዛት ባላቸው ሀገር በቀል ዛፎች ማለትም ዝግባ፣ የኮሶ ዛፍ፣ የሀበሻ ፅድ የተሞላ ነው፡፡
የቆጠር ገድራ የተፈጥሮ ደን ለረጅም ዘመናት ከሰው ንክኪ ተጠብቆ የቆየው በአካባቢው ኅብረተሰብ ነባር ባህል መሠረት የጥንት አባቶች ደኑ እንዳይቆረጥ በቃል ኪዳን/ጉርዳ/ ስለተሳሰሩ መሆኑም ተገልጿል፡፡
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጣ የጋዜጠኞች ቡድን በጉራጌ ዞን ከሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዱ የሆነውን የቆጠር ገድራ ጥብቅ ደንን ጎብኝቷል።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ዘውዱ ዱላ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት ከጥንት ጀምሮ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ደን መቁረጥ እንደ ወንጀል የሚቆጠር፤ በአካባቢው ባህል የሚያስቀጣ ነውር ተግባር ነው፡፡
ጥብቅ ደኑ ከ350 ሄክታር መሬት በላይ እንደሚሸፍን እና በውስጡ ከ18 በላይ የዛፍ ዝርያዎች እንደሚገኙም አንስተዋል።
የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ መሰረት አመርጋ በበኩላቸው የጉራጌ ህዝብ በስራ ወዳድነቱና ታታሪነቱ የሚታወቅ ከተፈጥሮ ጋር ትልቅ ቁርኝት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የሚገኘው የቆጠር ገድራ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ከ700 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት ሲሆን ህብረተሰቡ ደኑን ጠብቆ ያቆየበት መንገድ ከተፈጥሮ ጋር ላለው ቁርኝት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ደኑን በዘላቂነት ጠብቆ በማቆየት አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግናና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን በውስጡ ከያዛቸው የዛፍ ዝርያዎች ባለፈ የበርካታ ብዝኃ ህይወት መኖሪያ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የእዣ ወረዳ ደን እና አካባቢ ጥበቃ ልማት ጽህፈት ቤት የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ሂደት አስተባባሪ ብርሃኑ ብርሼ ናቸው።
እንደዚህ ዓይነት ጥብቅ ደኖች ሥነ ምሕዳርን በመጠበቅ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል።