የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ህብረ-ብሔራዊነትን ከማጠናከር ባለፈ ኢኮኖሚን የሚያነቃቃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ህብረ-ብሔራዊነትን ከማጠናከር ባለፈ ኢኮኖሚን የሚያነቃቃ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ህብረ-ብሔራዊነትን ከማጠናከር ባለፈ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት በየአካባቢው ያለውን ኢኮኖሚ እንደሚያነቃቃ ተመላክቷል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ዜጎች በአንድነት ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያቀርቡበት፣ የሚተዋወቁበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ብዝኃ ባህሎች፣ እሴቶችና ማንነቶች ደምቀው የሚታዩበት ነው።
ቀኑ በተለያዩ አካባቢዎች መከበሩ ለህብረ-ብሔራዊ አንድነትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የኢፌዴሪ የህገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የብዝኃ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ እሴቶችና ማንነቶች ተምሳሌት መሆኗን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ በየዓመቱ የሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን አብሮነትን የሚያጠናክር ከመሆኑም ባለፈ በዓሉ የሚከበርባቸው አካባቢዎች ያለው የቱሪዝም መስህቦች፣ ዕምቅ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ሃብቶችና ኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያስተዋውቅ ነው ብለዋል፡፡
በማዕከሉ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ተስፋዬ መገርሳ በበኩላቸው፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዕለቱ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ያላቸውን ባህል፣ እሴትና ልምድ የሚለዋወጡበት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን የሚያስተዋውቁበትና አብሮነታቸውንና አንድነታቸውን የሚያፀኑበት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በዓሉን ታሳቢ ያደረጉና ዘላቂ የሆኑ መሰረተ ልማቶች የሚዘረጉበት፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጠርበትና በአጠቃላይ በአካባቢው ያለው ኢኮኖሚ የሚነቃቃበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ ይከበራል።