መንግስት ለሰው ተኮር አጀንዳዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለአካታች ልማት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለሰው ተኮር አጀንዳዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለአካታች ልማት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት ለሰው ተኮር አጀንዳዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለአካታች ልማት እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በደሴ ከተማ የተመለከትናቸው የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት ግብይት ማዕከል እንዲሁም የእንጀራ መጋገራሪያ አዳራሽ ስራዎች የሕዝባችንን የየዕለት ችግሮች ለመፍታት ለምናደርገው ጥረት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
የግብይት ማዕከሉ ዋና ዓላማ አምራቾች እና ሸማቾችን በማገናኘት እና በመካከል ያለውን የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን ማረጋጋት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ማዕከሉ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን እና የእንስሳት ተዋጽኦዎች ግብይት እንደሚካሄድባቸውም ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ የቧንቧ ውሃ የእንጀራ መጋገራሪያ አዳራሽ ግንባታ እንጀራ በመጋገር ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ምርታማነትን በማስፋፋት የዜጎች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን ዓላማ ያደረገ ነው።
የብልጽግና ጉዟችን ሁሉንም ማኅበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ማኅበራዊ ፍትህን ያረጋገጠ ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ራዕይ የሚመራ ነው ሲሉም ገልጸዋል በመልዕክታቸው።