ቀጥታ፡

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት እየሰጠ ያለውን አገልግሎት አጠናክሮ መቀጣል እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን የ2018 ዓ.ም የአንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት፤ በመጀመሪያው ሩብ አመት 545 ሺ 491 ፓስፖርት ለዜጎች ተደራሽ ተደርጓል።

የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት (ኢ-ፓስፖርት) ደግሞ 14 ሺህ 818 ለሚሆኑ አገልግሎት ፈላጊዎች ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል።

ከገቢ አኳያም በሩብ ዓመቱ 11 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በዚህም ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን አስረድተዋል።

ሀሰተኛ ፓስፖርት ይዘው የተገኙ የአገር ውስጥና የውጪ ዜጎች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉንም አብራርተዋል።

በሩብ ዓመቱ 860 ሀሰተኛ ሰነድ ይዘው ፖስፖርት ለመውሰድ የሞከሩ የውጭ እና የአገር ውስጥ ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለው በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉንም ገልጸዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ሰላማዊት ገለጻ፤ በሩብ ዓመቱ በድንበር አካባቢ በተከናወነ የቁጥጥር ሥራ 16 ሺህ 465 የሚሆኑ የውጭና የሀገር ውስጥ ዜጎች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡና ከኢትዮጵያ ሊወጡ ሲሉ ተይዘዋል።

በተቋሙ ሪፎርም ከተደረገ ወዲህ ከተገልጋዮች የሚነሱትን ጥያቄዎች በሟሟላት በመደበኛ በስድስት ወር ይሰጥ የነበረውን ፓስፖርት በሁለት ወራት እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርም ሕገ-ወጥነትን በመከላከል ዙሪያም የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ የዲጂታል አሰራር ሥርዓትን በመከተል መስጠት የጀመረውን አገልግሎት ይበልጥ ሊያጠናክር ይገባል።

ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ፣ ቅርንጫፎቹን ማስፋፋት እንዲሁም ተቋማዊ ደህንነት ለማጠናከር የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ ማጠናክር እንደሚኖሩበትም አስገንዝበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ ሕግን በማስከበር ላይ ውጤታማ ሥራ በማከናወኑ የሚበረታታ እና በጠንካራ ጎን የሚጠቀስ ነው።

ሕገ-ወጥነትን መከላከል ላይ የጀመራቸውን ሥራዎች ማጠናከር እንዲሁም የድንበር አካባቢ ቁጥጥር ሥራዎችን በትኩረት መከወን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም