ቀጥታ፡

የመንግስት አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመስጠት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ የመንግስት አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመስጠት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመርያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

ሚኒስቴሩ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ፣ በዲጂታል መታወቂያና በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና አበረታች ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡  

በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ከተቋማት ጋር በመቀናጀት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች በማከናወን ላይ ነው።


 

ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴሩ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የመንግስትና የንግድ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር ሀገራዊ ኢ-ኮሜርስና የኢንተርኔት የንግድ ግብይት ስርዓትን ለማሳደግ ምን እየሰራ እንደሆነ ጥያቄ አቅርቧል።

የኢትዮ-ኮደርስ መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት ስልጠና ለመስጠት የሚኒስቴሩ ድጋፍና ክትትል ምን ይመስላል በሚለው ላይም ማብራሪያ ጠይቋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) የተቋማቸውን አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ ባለፉት ሶስት ወራት በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡  

በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከተቋማት ጋር በመቀናጀት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች መከናወናቸውን በመግለጽ።

በዚህም 10 የንግድ ተቋማት ወደ ኤሌክትሮኒክ ግብይት መግባታቸውን፣ ሶስት የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማሳለጫ ፕላት ፎርሞችን በማዘጋጀት ለ56 አይሲቲና ዲጂታል ኢንዱስትሪዎች ብቃት ማረጋገጫ መስጠት መቻሉን ጠቅሰዋል።


 

በሌላ በኩል በኦንላይን የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶችን በሚመለከት የተያዘውን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉንም አስታውቀዋል።

ከዲጂታል መታወቂያ ጋር በተያያዘ በ2018 የመጀመርያ ሩብ ዓመት አምስት ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮ-ኮደርስ መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት ስልጠና ባለፉት ሶስት ወራት ከ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያነሱት።

ከተሞችን በዲጂታል አድራሻ ስርዓት ለማካተት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፤ በሩብ ዓመቱ የአምስት ከተሞች ትግበራን የማጠናቀቅ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ሀገራዊ ኢኖቬሽን ምርምርና ቴክኖሎጂን በሚመለከት በሩብ ዓመቱ ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን ነው ያስታወቁት፡፡


 

እንዲሁም 205 ችግር ፈቺ ምርምሮችን በምርምር እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማከናወን መቻሉንም አንስተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፤ ሚኒስቴሩ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማድረግ የተቋማትንና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲሰጡ በቅንጅት መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በምታደርገው ጉዞ ቴክኖሎጂ አስፈላጊ በመሆኑ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የሚደረገው ቅንጅታዊ አሰራር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

ተቋማት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለመጠቀም ዝግጁ እንዲሆኑ ማገዝ እንደሚገባ አሳስበው፤ ቴክኖሎጂውን አስመልክቶ ለተቋማትና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶር) በመጨረሻም በቋሚ ኮሚቴው የተነሱ ክፍተቶችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም