ቀጥታ፡

ሶስተኛው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት በአዲስ አበባ ይካሄዳል 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡- የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የ2025 የሚዲያ ሽልማት ህዳር 20 እና 21 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ይደረጋል። 

የሽልማት ስነ ስርዓት “ ውጤታማ የአየር ንብረት ዘገባ ደህንነቱ ለተረጋገጠ፣ ጠንካራ እና የተረጋጋ ቀጣና” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከናወን ነው። 

ኢጋድ ቀጣናዊ ሁነቱን ያዘጋጀው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ነው። 

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያና የአፍሪካ ኢምፖርት እና ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪኤግዚም ባንክ) ለፕሮግራሙ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቋል። 
 
የዚህ ዓመት ሽልማት በአፍሪካ ቀንድ ውጤታማ የአየር ንብረት ትርክትን ለቀረጹ ጋዜጠኞች እና የፊልም ባለሙያዎች እውቅና የሚሰጥ ነው። 

የሁለት ቀን ሁነቱ የአየር ንብረት ጠንካራ ዘገባዎች እና ሀሳቦች የሚቀርቡበት እንዲሁም ቀጣናዊ ትብብር ጎልቶ የሚታይበት መሆኑን ኢጋድ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል። 

የ2025 የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት በ10 ዘርፎች የሚከናወን ነው።

የህትመት ጋዜጠኝነት፣ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት፣ የቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት፣ ዲጂታል ሚዲያ፣ ፎቶ ግራፈር፣ ሀገር በቀል/ ብሄራዊ ቋንቋ ዘገባ፣ የዓመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ/ የይዘት ቀራጭ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እና የእድሜ ዘመን ሽልማት የሽልማት ዘርፎቹ ናቸው።

የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት ከእ.አ.አ 2023 ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኝ ዓመታዊ ሁነት ነው።

የ2023 ሽልማት በጅቡቲ፣ የ2024ቱ በኬንያ ናይሮቢ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም