ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የደረሰችበትን እድገት የሚየሳዩ እና ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች እየተገነቡ ነው - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ

ባህር ዳር፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን እድገት የሚያሳዩ እና ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች እየተገነቡ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ አስታወቁ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማሕበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የባሕር ዳር ስታዲየምንና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ተመልክተዋል።


 

የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሽዊት ሻንካ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የስፖርት ልማት፣ ውጤታማነትን በሚያረጋግጥ አግባብ እየተከናወነ ነው።

ከለውጡ ወዲህ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የስፖርት ልማት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ጥናት ላይ የተመሰረተ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ህፃናትና ታዳጊዎች ላይ በመመስረት ተተኪና ብቃት ያላቸው ስፖርተኞችን በሁሉም ዘርፎች ማፍራት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችን ችግር በመፍታት ውጤታማ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመላ ሀገሪቱ በርካታ መካከለኛና አነስተኛ ስታዲየሞች መገንባት ተችሏል ብለዋል።


 

እንዲሁም ነባርና አዳዲስ ታላላቅ ስታዲየሞች ግንባታ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቀ አግባብ እየተገነቡ መሆኑን ጠቁመው መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

የባህር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ አርባ ምንጭ፣ አደይ አበባ እና ሌሎች ታላላቅ ስታዲየሞች የፊፋንና ካፍን ደረጃ በጠበቀ መንገድ እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰው ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው በሙያ ታግዘው እየተሰሩ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በቀጣይ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ የሚያስችሉ ብቃት ያላቸው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

መንግስት ለስፖርት ልማት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱንና እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞች የኢትዮጵያን ገፅታና እድገት በሚያሳይ አግባብና ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


 

በኢትዮጵያ የስፖርት ልማት ዘርፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መንገድ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማሕበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ(ዶ/ር ) ናቸው።

ስፖርት ለኢኮኖሚ እድገት ካለው ፋይዳ ባሻገር ማህበረሰቡ በትርፍ ጊዜው መዝናናት እንዲችል ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

የባህር ዳር ስታዲየም ግንባታ ዓለም አቀፍ መስፈርት ባሟላ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ማረጋገጥ እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በቀጣይ የስታዲየሙ ጥላ በትብብር የሚሰራበትን ሁኔታ ስራ አስፈፃሚው ሊያመቻች ይገባል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ስፖርት ጨዋታ ብቻ አይደለም ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ስፖርት የሀገር ሉዓላዊነት፣ ዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ መስተጋብርና ሌሎች ሁሉን አቀፍ ጉዳዮችን የያዘ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ ልማቶች የበለጠ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና ለዚህም ምክር ቤቱ ተገቢውን እገዛና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ እርዚቅ ኢሣ በበኩላቸው፤ የባሕር ዳር ስታዲየም የካፍና ፊፋ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ እየተገነባ መሆኑን ጠቁመው ትላልቅ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንዲችል ሆኖ በጥራት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለስታዲየሙ የሚያስፈልገው የመጠለያ ስራም በቀጣይ የክልሉና የፌደራል መንግስት በትብብር እንደሚሰሩበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም