ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሽፕን የመንግስት መለያ ማድረግ የሚያስችሉ ተቋማትና ሕጎች ተተግብረዋል - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ኢንተርፕርነርሽፕን የመንግስት መለያ ማድረግ የሚያስችሉ ተቋማትና ሕጎች መተግበራቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጠባቂነትን አስወግዶ በሀሳብ ሀብት መፍጠር እንደሚቻል ያሳየ ተቋም መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት "በጋራ እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ ተከፍቷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን(ዶ/ር)፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች ተሳታፊዎች በመክፈቻ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተዋል።

ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ስሟን ከፍ ያደረጉ አንቱ የተባሉ ምስጉን፣ ታታሪ ኢንተርፕርነሮችስ ስትፈጥር ቆይታለች።


 

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሽፕን የመንግስቷ መለያ ማድረግ የሚያስችሉ ተቋማትን የገነባችው፣ ሕጎችን ያወጣችው ባለፉት ሰባት ዓመታት ነው ብለዋል።

በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት የኢንተርፕርነርሽፕ ሥነ ምህዳርን ተቋማዊ ማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ መደረጉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሀሳብ ብዝሃነት ጸጋ ለሀሳብ ፈጠራ ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጠባቂነትን አስወግዶ በሀሳብ ሀብት መፍጠር እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

በዚህም ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሽፕን የመንግስት መለያ ማድረግ የሚያስችሉ ተቋማትና ሕጎች ተተግብረዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የኢንተርፕርነሮች መፍለቂያ ትሆናለች ያሉት ሚኒስትሯ፤ መንግሥት የኢንተርፕርነርሽፕ ምህዳሩን ምቹ ማድረጉን ገልጸዋል።

ሀሳብ ካለ ሀብት መፍጠር እንደሚቻል አምናለሁ ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል እምቅ ሀገራዊ አቅም፣ ፖሊሲና ተቋም ተገንብቷልም ብለዋል።

የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ ኢንተርፕርነር መሆንና እንዴት እንደምትሆን በግልጽ አስቀምጧል ነው ያሉት።


 

የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የኢንተርፕርነርሽፕ ሁነቶችን በማዘጋጀት ብራዚልን በመቅደም ከዓለም አንደኛ ሆናለች ብለዋል።

ኢንተርፕርነሮች የፈጠራ መፍትሔዎችን ወደ መሬት የሚቀይሩ፣ ምኞትን የሚያሳኩ፣ አይቻልምን ችለው የሚያሳዩ ፈር ቀዳጅ ባለራዕዮችና ከዋኞች ናቸው ነው ያሉት።

ኢንተርፕርነሮች ሀገር ሰሪዎች መሆናቸውን ጠቁመውም በዘንድሮው 12ኛው የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት ስልጠናዎች፣ የፈጠራ ሀሳብ ውድድሮችና ጥናቶች ይከናወናሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚወሰን ሳይሆን ድንበር ተሻጋሪ ሥራ ጀምረናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የመጨረሻ ግባችን አይበገሬ ማህበረሰብ፣ ዜጋና ሀገር መገንባት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም