የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና በነባሮቹ ላይ እሴት በመጨመር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና በነባሮቹ ላይ እሴት በመጨመር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ የቱሪዝም ሚኒስቴር አዳዲስ መዳረሻዎችን በማልማትና ነባሮቹ ላይ እሴት በመጨመር ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራትን እንዲያጠናክር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትን የ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ገምግሟል።
ኢትዮጵያ ያላትን ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሃብቶች ከማልማት ባሻገር በስፋት ለማስተዋወቅ የተጀመሩ ሥራዎች የኢትዮጵያን ምድረ-ቀደምትነት የሚያረጋግጡና የአገርን ገጽታ የሚገነቡ ስለ መሆናቸው ተነስቷል።
መንግስት ዘርፉን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ማድረጉ በራሱ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱም ተገልጿል፡፡
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመሩ የገበታ ለአገር፣ ገበታ ለትውልድና ገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች ለዘርፉ መነቃቃት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው ተነግሯል።
የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለሚኒስቴሩ ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከል የገበታ ፕሮጀክቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ ሚኒስቴሩ በራሱ አቅም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማት ያከናወናቸው ተግባራት ይጠቀሳሉ።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው በቋሚ ኮሚቴው ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ጊዜ ተቋማቸው በሩብ ዓመቱ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ተመራጭና ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን አብራርተዋል።
ከእነዚህ ውስጥ የጅማ አባጅፋር ቤተ-መንግስት ጥገናና ዕድሳት፣ የባሌ ብሄራዊ ፓርክ መዳረሻ ልማትና ፕሮጀክት፣ የጂኦ ፓርኮች ልየታና ልማት ስራን ለአብነት አንስተዋል።
በነባር መዳረሻዎች ላይ እሴት በመጨመር ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ በፋሲል አብያተ መንግስታት ''ሕይወት በቤተ መንግስት'' የተሰኘ ትዕይንት መዘጋጀቱን አንስተዋል።
በዚህም በዓብያተ መንግስታቱ ሲከወኑ የነበሩ የአስተዳደርና የፍትህ፣ የግብር ማብላት ስርዓቶችን ጨምሮ የኪነ-ጥበብና የዕደ-ጥበብ ሥራዎች እሴቶቻቸው ተጠብቀው እንዲቀርቡ ተደርጓል ብለዋል።
ጥንታዊውን የደጋ እስጢፋኖስ ገዳም ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ይዞታውን ጠብቆ ለጎብኚዎች ተደራሽ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ ከባቡር ትራንስፖርት ጋር ያላትን ቁርኝት በሚያሳይ መልኩ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎችን ለአብነት አንስተዋል።
በተያዘው ዓመት የቱሪዝም ሃብቶችን ለይቶና ደረጃ አውጥቶ የመዳረሻ ልማት ለማከናወን ከክልሎች ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።
በተጨማሪ ቱሪዝም በአጠቃላይ የአገር ወስጥ ምርት ያለው ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ ጠይቋል።
ሚኒስትሯ ዘርፉ ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት ዕድገት ያለውን ሚና በአግባቡ ለመለየት ባለፈው ዓመት የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አሻ ያህያ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በተለየም የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት በጥንካሬ የሚወሰዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሃብት ባለቤት እንደመሆኗ ይህን ሃብት ገልጦ የማሳየት፣ የመጠቀምና የማስተዋወቅ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በቱሪስት መዳረሻ ልማትና እሴት መጨመር ላይ የጀመራቸውን ተግባራት የበለጠ እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።
ሚኒስቴሩ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከቅርስና የዱር እንሰሳት ጥበቃ ጋር በተያያዘ የሚታዩ ክፍተቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት መፍታት አለበት ሲል ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።