ቀጥታ፡

የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር በጋራ መልማትና መስራትን በማንበር ትስስርን አጠናክሯል

ሰመራ፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል መከበር በጋራ መልማትና መስራትን በማንበር ትስስርን ማጠናከር መቻሉን የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አሲያ ከማል ተናገሩ።

20ኛውን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ የአፋርና የአማራ ክልሎች አጎራባች ዞኖች በጋራ በመሆን በአፋር ክልል ዱለቻ ወረዳ አክብረዋል።

በዓሉ የተከበረው የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እና የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አሲያ ከማልን ጨምሮ የአርጎባ እና ዱለቻ ወረዳ ነዋሪዎች በተገኙበት ነው።

የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሲያ ከማል በዚሁ ወቅት እንደገለፁት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል መከበር ብሔሮችና ብሔረሰቦች የጋራ የሆኑ እሴቶች እንዲያጠናክሩ እያገዘ ነው።

በዓሉ የጋራ እሴቶችን በማጎልበት ክልሎች በአንድ ላይ ሆነው በመስራትና በልማት ግንኙነታቸውን ማጠናከር መቻሉን ተናግረዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በማጎልበት በአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ዳብሮ በልማታዊ ስራዎች መደጋገፋቸው ተጠናክሯልም ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አብሮነትን በማጠናከር ለትብብር የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

የጋራ ትርክቶችን በማሰረፅ ረገድም በዓሉ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት መጓዝ እንደምንችልና የተጋመደውን ወንድማማችነት እና እህትማማችነት በስራና አብሮ በመልማት ማጠናከር ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም