የጸጥታ ሀይሉ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ወቅቱ በደረሰበት ክህሎትና እውቀት ራሱን ማሳደግ ይገባዋል - ኢዜአ አማርኛ
የጸጥታ ሀይሉ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ወቅቱ በደረሰበት ክህሎትና እውቀት ራሱን ማሳደግ ይገባዋል
ቦንጋ፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ የጸጥታ ሀይሉ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ወቅቱ በደረሰበት ደረጃ እውቀትና ክህሎቱን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።
“ከጂኦስትራቴጂካዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና” በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉን የፀጥታ ሀይል ሙያዊ እውቀትና ክህሎት የሚያሳድግ የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሀብታሙ አለሙ በወቅቱ እንዳሉት፤ የጸጥታ ኃይሉ የክልሉን ጸጥታና ልማት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ይገኛል።
ይህን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣትም የጸጥታ አካላቱን እውቀትና ክህሎት ወቅቱ በደረሰበት ደረጃ ይበልጥ በማሳደግ ለህዝቡ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችልበትን አቅም ማሳደግ ላይ መስራቱን አንስተዋል።
ተልዕኳችን ጥልቅ ራዕያችን ሰፊ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ሀላፊው የፖሊስ አመራሩንና አባሉን አቅም በመገንባት በህዝብ ዘንድ የሚከበርና የሚታመን የፖሊስ ተቋም ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የክልሉ ፖሊስ መዋቅር በርካታ ሪፎርሞችን በማከናወን የተሻለ ልምድና አቅም ያለው ሰራዊት መገንባት መቻሉንና በቀጣይም ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በክልሉ የተመዘገቡ ለውጦችን ለማስቀጠል የጸጥታ ኃይሉን ማጠናከር ላይ መስራት አስገዳጅ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወንድሙ ኩርታ ናቸው።
ከዚህ የተሻለ ለውጥ ለማምጣትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የላቀ ቁርጠኝነትና የዓላማ ፅናት ያነገበ የፖሊስ አባል ያስፈልጋል ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ የህግና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲል አሻግሬ ስልጠናው ሀገራዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በስራ ላይ ያሉ እንቅፋቶችን በመፍታት ህዝብን የበለጠ ለማገልገል እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የፖሊስ አመራሮችና አባላት እየተሳተፉ ነው።