ቀጥታ፡

በክልሉ በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን በመለየትና በማልማት ለስራ ፈጣራ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቷል

ባሕር ዳር፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን በመለየትና በማልማት ለስራ ፈጣራ የሚያውል  ታታሪ ትውልድ ለመገንባት ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ከ260ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የክልሉ ስራና ክሕሎት ቢሮ አስታውቋል።

ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በጋራ እንገነባለን በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፍ የስራ ዕድል ፈጠራ ሳምንት የመክፈቻ መርሃ ግብር ዛሬ አካሂዷል።


 

የቢሮ ኃላፊው ስቡህ ገበያው(/)፤ የዓለም አቀፍ የሥራ ፈጠራ ሳምንትን ስናከብር በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን በመለየትና በማልማት ለስራ ፈጣራ የሚያውል ታታሪ ትውልድ ለመገንባት በማለም ነው ብለዋል።

ቢሮው የክልሉን ፀጋ በመለየትትና በማልማት ለስራ ፈጠራ ለማዋል ሲሰራ መቆየቱን አውስተው፤ በሂደቱም ስራ ፈላጊዎችን በመመዝገብና ፍላጎታቸውን መሰረት በማድረግ አሰልጥኖ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል።

የዛሬው መርሃ ግብርም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የተጀመሩ የስራ ፈጠራ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል መሆኑን አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተያዘው አቅድ ውስጥ ባለፉት አራት ወራት ለ265ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የገለጹት ደግሞ  የቢሮው ምክትል ኃላፊ አወቀ ዘመነ ናቸው።

የስራ ዕድሉ የተፈጠረው በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በዕደ ጥበብ፣ በብረትና እንጨት ስራና ሌሎች ዘርፎች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለስራ ዕድል ተጠቃሚዎችም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በመደበኛና በተዘዋዋሪ ብድር፣ ከ4ሺ 300 ሄክታር በላይ መሬትና 719 ሼዶች ተገንብተው መተላለፉን አስታውቀዋል።

አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የተካሄደው ቅንጅታዊ አሰራር ያስገኘው ውጤት ነው ብለዋል።

በኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት የአማራ ክልል ፕሮግራም አስተባባሪ ይበልጣል ኤልያስ በበኩላቸው፤ በአማራ ክልል የስራ ፈላጊዎችን እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ስልጠናው ከክልል እስከ ወረዳ ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቢሮው አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም