የፀጥታ ሀይሉ የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታን አስተማማኝ በማድረግ ልማትና ብልጽግና እንዲፋጠን አድርጓል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታ ሀይሉ የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታን አስተማማኝ በማድረግ ልማትና ብልጽግና እንዲፋጠን አድርጓል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ የፀጥታ ሀይሉ የጋምቤላ ክልልን ሰላምና ፀጥታን አስተማማኝ በማድረግ ልማትና ብልጽግና እንዲፋጠን ማድረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
“ከጂኦስትራቴጂካዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና” በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉን የፀጥታ ሀይል ሙያዊ እውቀትና ክህሎት የሚያሳድግ የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ በጋምቤላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበቅ ለክልሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ግብ መሳካት የጸጥታ አካላት ሚና የላቀ ነው።
የክልሉ ፖሊስ የክልሉን ሰላም ለማጽናትና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የውስጥና ድንበር ተሻጋሪ የፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን በመከላከል ረገድ ያለው ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የፀጥታ አካላትን በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ-ልቦና በመገንባት ኃላፊነታቸውን የበለጠ እንዲወጡ የአቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በዕለቱ የተጀመረው የአቅም ግንባታ ስልጠና የፀጥታ አካላቱ ዘመናዊ የውትድርና ሳይንሱን በመያዝ ለክልሉም ሆነ ለሀገር ሰላምና ብሔራዊ ጥቅም መከበር ከመቼውም ግዜ በላይ እንዲተጉ አቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡጉላ ኡጁሉ በበኩላቸው ኮሚሽኑ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበቅ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለክልሉ የፀጥታ አመራሮችና ለአባላት እየተሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና አለም አቀፍ ጂኦ-ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ተረድቶ ኃላፊነቱን በብቃትና በአሸናፊነት መንፈስ የሚወጣ ሃይል ለማፍራት መሆኑን ተናግረዋል።
በዕለቱ በተጀመረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የፀጥታ አመራሮችና አባላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።