በባሌ ዞን ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩ 112 አርሶ አደሮች እና ማህበራት የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩ 112 አርሶ አደሮች እና ማህበራት የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ
ሮቤ፤ ህዳር 8/2018 (ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩ 112 አርሶ አደሮች እና ማህበራት የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠቱን የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የተደረገላቸው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለተሻለ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው ወደ ኢንቨስትመንት ተሸጋገሩት አርሶ አደሮች ገልጸዋል።
የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ኢብሮ እንዳሉት በዞኑ ወደ ኢንቨስትመንት በመሸጋገር እውቅና ያገኙት 112 አርሶ አደሮች እንዲሁም ኢንተርፕራይዞች ናቸው።
ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮችና ኢንተርፕራይዞች ባለፉት ዓመታት በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ከመሆን ባሻገር ከ422 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ኢንቨስተሮቹ ወደ ስራ ሲገቡ 5 ሺህ 600 ለሚጠጉ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደሚፈጥሩም አክለዋል።
በዞኑ አርሶ አደሩ በመደበኛነት ከሚያመርተው ሰብል በተጓዳኝ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት የሚሸጋገሩ አርሶ አደሮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩት አርሶ አደሮችና ማህበራት በሚሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ የመሬት አቅርቦትና ሌሎች የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደሚደረግላቸውም አመልክተዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን ወደ ኢንቨስትመንት ከተሸጋገሩ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ኮርሳ አሰፋ፤ በግብርና በመሰማራት በሚያመርቱት ስንዴና ሌሎች ሰብሎች ልማት 9 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ኢንቨስትመንት በመሸጋገራቸው 10 ሄክታር መሬት በኢንቨስትመንት ማበረታቻነት ማግኘታቸውን ገልፀዋል።
በአካባቢው ከሚመረተው የስንዴ ምርት በተጨማሪ ገበያ ተኮር የሆኑ ቅመማ ቅመም በማምረት በሚያገኙት ገቢ 10 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር ሐጂ ኢብራሂም ከድር ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በኢንቨስትመንት ማበረታቻነት የተሰጣቸው መሬትና የእውቅና ሰርተፊኬት ለተሻለ ሥራ እንዳነሳሳቸውም አክለዋል።
አቶ ግርማ ከተማ በበኩላቸው በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ውጤታማ በመሆን ባስመዘገቡት 2 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ የዛሬዎቹን ሳይጨምር 200 የሚሆኑ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ባስመዘገቡት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ካፒታል ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸው ተገልጿል።