ቀጥታ፡

በክልሉ ጠንካራ የፖሊስ ተቋምና አመራር ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት -ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህርዳር፤ ህዳር 8/2018 (ኢዜአ)፦ በክልሉ ጠንካራ የፖሊስ ተቋምና አመራር ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ “ከጂኦ ስትራቴጂክ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና" በሚል መሪ ሃሳብ ለከፍተኛና መካከለኛ የፖሊስ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ጂኦ ስትራቴጂ የሚያስገኘውን ጥቅምና ተግዳሮት ላይ ለሁሉም ህብረተሰብ ሰፊ ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሰራ ነው።


 

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በቅርበት የምትገኝና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ባለቤት በመሆኗ ከአለም ማህበረሰብ በእጅጉ የተሳሰረ የጂኦስትራቴጂ እድልና ተግዳሮት ያላት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም አገራችን ያወጣችውን የጂኦስትራቴጂ ፖሊሲና እቅድ በአግባቡ በመምራት ያለንን እድል ወደ ድል በመቀየር ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ማስጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል።

ፖሊስ ወንጀልን በመከላከልና የክልሉን ሰላም በማፅናት ለብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ጠንካራ የፖሊስ ተቋምና አመራር ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው፤ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

የፖሊስ አመራሩና አባሉ ጂኦስትራቴጂ የሚያስገኘውን ጥቅም፣ ሊያጋጥም የሚችለውን ተግዳሮትና የአለምን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ በመገንዘብ ራሱን ለተልዕኮ ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸዋል።


 

የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሚሰጠው ስልጠና የፖሊስ አመራሩን ለላቀ ተልዕኮ ለማዘጋጀት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዚህም የክልሉን ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብና ሰላምን ለማጠናከር የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችል መሆኑን ተገንዝቦ ስልጠናውን በአግባቡ መከታተል ይገባል ብለዋል።

በስልጠናው ላይ የክልሉ፣ የሰሜን ጎጃም ዞንና የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የፖሊስ አመራሮች መሳተፋቸውም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም