ቀጥታ፡

ሕግን በማስከበር ሰላምን ለማፅናት የፀጥታ ኃይሉ ሃላፊነት የጎላ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

‎ሀዋሳ፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሰላምን በዘላቂነት በማፅናት ረገድ የፀጥታ ኃይሉ ሃላፊነት የጎላ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

“ከጂኦስትራቴጂካዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና” በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ለሚገኙ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

በስልጠና ማስጀመሪያው ላይ የተገኙት ርዕሰ መስታዳድር ደስታ ሌዳሞ ኢትዮጵያ በቀደሙ ጊዜያት የሥልጣኔ ማማ ማሳያ፣ ገናና ስም የነበራትና በኢኮኖሚም ተወዳዳሪ እንደነበረች አስታውሰዋል።

በአሁን ወቅትም የነበራትን ክብርና ከፍታ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በዚህ ሂደት ውስጥ የፀጥታ ኃይሉ የህዝብን ሠላምና ፀጥታ በማጠናከር በኩል ሃላፊነቱ የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

ኢትዮጵያን ለማሳነስ ሌት ተቀን የሚሰሩ አካላትን እንቅስቃሴ በመረዳት ሁላችንም ለሀገር ጥቅም በጋራ ዘብ መቆም ይኖርብናል ያሉ ሲሆን በዚህ ረገድ የፀጥታ ኃይሉ ሚና የማይተካ መሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ ፖሊስም ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የህዝብንና የልማት ፕሮጀክቶችን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተስፋዬ ዴቢሶ በበኩላቸው ስልጠናው የፀጥታ ኃይሉ ወጥና የተስተካከለ ቁመና እንዲላበስ ከማድረግ ባሻገር ሀገራዊና ክልላዊ ግንዛቤውን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

የክልሉ ፖሊስ ህዝብን ከማገልገልና ሕግና ሥርዓትን ከማስጠበቅ አንፃር የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡና በስኬት እንዲወጣ በኮሚሽኑ በኩል የሪፎርም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በስልጠናው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሰው ሃብት ስራ አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደርቤ ገቢሳ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትን በማፋጠንና በማንሰራራት ሂደት ውስጥ መሆኗን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ሰላምና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፖሊስ ሠራዊት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው ሥልጠናው በፌዴራል ፖሊስ ደረጃ የተጀመረው የሪፎርም ሥራ ወደ ክልሎች እንዲወርድ ያግዛል ብለዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፖሊስ ተቋም እንዲኖር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ዛሬ ለፖሊስ አመራሮችና አባላት መሰጠት የተጀመረው ስልጠና ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም