ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የተከተለችው ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለጋራ ትርክት ግንባታ ፋይዳው የጎላ ነው

ጎንደር፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የተከተለችው ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የጋራ ትርክትን ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለጸ።

"በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዛሬ በጎንደር ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።፡

በፓናል ውይይቱ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አላምረው አበራ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ ፀንቶ እንዲቀጥል በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማጠናከር ወሳኝ ነው።

ሀገሪቱ የበርካታ ብዘሃ ሃይማኖት፣ ባሕልና ታሪክ ባለቤት እንደመሆኗ ይህን እሴት በመጠቀም  ለሰላም፣ ለልማትና ለብልጽግና ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተከተለችው ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት ለጋራ ትርክት ግንባታ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት አላምረው የበዓሉ መከበር ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ሀገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ከዳር መድረስም እንዲሁ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር  ባምላክ  ይደግ(ዶ/ር) ባቀረቡት ጽሁፍ እንደገለጹት፤  የፌደራሊዝም ሥርዓት ብዝሀነትን ለማስተናገድ ወሳኝ መሳሪያ ነው ፡፡

ጠንካራ የሞራል ልእልና ያለው የፖለቲካ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ዜጎችን በእውቀት፣ በአመለካከትና በአስተሳሰብ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የዛሬው በዓል ዓላማም ህገ መንግስታዊና ፌደራላዊ ሥርዓቱ  ያለውን ፋይዳ ለማስገንዘብ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የጋራ ትርክት ግንባታ ያለውን አስተዋጽኦ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ ግንባታ በጉልህ ማየት ችለናል ያሉት  የዞኑ የመንግስት ሠራተኛ የሆኑት አቶ ሷልህ ኑርሁሴን ናቸው፡፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል መከበሩ አንዱ የሌላውን ባሕል እምነትና እሴት በማክበር  ለሀገረ መንግስት ግንባታው መጠናከር መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

ሌላው ተሳታፊ  ወይዘሮ ወይንሸት አያሌው፤ የበዓሉ መከበር ሕብረብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ለውጤት ለማብቃት አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና ከተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ  ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም