ቀጥታ፡

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ። 

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የክልሉን መሶብ (ኮራ) የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሰመራ ሎጊያ ከተማ  ስራ አስጀምረዋል።

በመርኃ ግብሩ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) እንዲሁም  የፌደራል እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በዚሁ ወቅት፤ ለአገልግሎቱ መጀመር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

በክልሉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

10ኛው የከተሞች ፎረም በሰመራ ሎጊያ ከተማ መከናወኑ ለከተማዋ ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለከተሞች ብዙ ትርጉም አለው ብለዋል። 


 

አገልግሎቱ ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት በተቀላጠፈ ሁኔታ የሚያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በሰመራ ሎጊያ የተገነባው የመሶብ ማዕከል የሚደነቅ ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ መልካም አስተዳደርን በማስፈን በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአንድ ቦታ በርካታ አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

መሶብ የተሳለጠ ሰው ተኮር አገልግሎት የሚሰጥበት ማዕከል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር) ናቸው።


 

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ እንዲሁም የአገልግሎት ልህቀት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ዜጎች ከመንግስት የሚፈልጉትን አገልግሎት በተቀላጠፈ ሁኔታ የሚያገኙበት የኢትዮጵያ ማንሰራራት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፋር ክልል በዚህ ረገድ ያቋቋመው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚደነቅ ስራ መሆኑን ገልጸው ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም