የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ተቋም ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ተቋም ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ተቋም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ ቤቱን ቀድሞ ከነበረበት ቀይሮ ወደ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ሕንፃ በተዛወረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚሁ ወቅትም የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአምስት ዓመት ውስጥ አሁን በሚገኝበት ደረጃ ላይ መድረሱ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ የሮቦቶችን ሶፍትዌር ብቻ ሳይሆን ውጫዊ የአካል ክፍልን (ሃርድዌር) መሥራት ጀምሯል ብለዋል።
ድሮን ማምረት ብቻ ሳይሆን የማነጋገር ዐቅም እየፈጠረ ያለ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ ደረጃ የሚወዳደር አሠራርን የሚከተል መሆኑን ጠቁመው፤ በርካታ ምርቶችን አውጥቷል ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ የጡት ካንሰር ልየታ ላይ ትልቅ ውጤት ማምጣት መቻሉን እና ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርቲፊሻል ዐዋቂዎች ዘንድ ተቀባይነት ብሎም የባለቤትነት መብት ያገኘ ሥራ ነው ብለዋል።
በግብርና ዘርፍም የቡናና የሌሎች አዝርዕቶች በሽታ የሚለይ ፕሮዳክት መመረቱን በመጠቆም ለዚህም ባለቤትነት መብት መኖሩን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል መሶብ የሚባለውን በአንድ ማዕከል ከ100 በላይ አገልግሎቶች የሚሰጠውን ሲስተም የገነባው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መሆኑን አስታውቀዋል።
ገንዘብ ሚኒስቴር፣ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽንን ጨምሮ ተቋማት አሠራሮቻቸውን ለማዘመን የሚገለገሉባቸው በርካታ ሲስተሞችን መገንባት መቻሉን አንስተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ሞቶ ኤ አይ ለሁሉም ስለሆነ፤ ከዚህ አንጻር አንዱ ማሳያ ክላውድ ኮምፒቲንግ መሆኑን አንስተዋል።
ለምሳሌ ከዳታ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ የአንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ሦስተኛ ሰው ሳያስገባ ከሌላኛው ቋንቋ ተናጋሪ ጋር መግባባት የሚችልበትን መንገድ፣ በጽሑፍ የገባን መልዕክት ወደ ድምጽ የመቀየር፣ በድምጽ ያለ መልዕክትን ወደ ጽሑፍ የመቀየርና መሰል አገልግሎት ለመስጠት በሺህ ሰዓቶች የሚቆጠሩ ኦዲዮዎችን ዳታዎች በማስገባት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የግብርና ሪቮሉሽን አንድ ሁለት ሦስት እያለ መጥቷል እኛ እዛ ውስጥ አልነበርንም፤ ቴክኖሎጂካል ሪቮሉሽን ነበሩ፣ ኢንደስትሪያል ሪቮሉሽኖች ነበሩ፤ በእነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያ በሬና ሰውን ማላቀቅ ሳትችል የኖረችበት ዋናው ምክንያት አዲስ ዕውቀት፣ አዲስ ልምምድ፣ አዲስ ፈጠራ ሲፈጠር ያንን ነገር ለማወቅና ለመከተል የነበረው ጉጉት፣ ዝግጁነት እና እሳቤ አናሳ ስለነበረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እዚህ ላይ ለመተካከል ሳይሆን ጥሩ ተከታይ ለመሆን እንኳ በእጅጉ ይቀረን ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ሁኔታው መቀየሩን በአጽንኦት አስረድተዋል።
ስለዚህ ብንፈልግም ባንፈልግም ራሳችንን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሂደት ውስጥ ማስገባት ካልቻልን ደረጃው የትም ቦታ ይሁን እንደ ሀገር እንደ ከዚህ ቀደሙ ከትላልቅ ሪቮሉሽኖች ወደ ኋላ እንቀራለን ሲሉ አስገንዝበዋል።