ቀጥታ፡

ጣልያን በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-ጣልያን የቤቶች ልማትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራች እንደምትገኝ በኢትዮጵያ የጣልያን ኤምባሲ የንግድ ኮሚሽነር ክላውዲዮ ፓስኩዋሉቺ ገለጹ።

ኮሚሽነር ክላውዲዮ ፓስኩዋሉቺ ጣልያን እና ኢትዮጵያ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ቢኖራቸውም የንግድ ትብብራቸው የሚፈለገውን ያህል እንዳላደገ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ጣልያን ወደ ኢትዮጵያ የምትልካቸውን ምርቶች እንዲሁም ቡና እና ማዕድናትን ጨምሮ ከኢትዮጵያ የምታስገባቸውን ስትራቴጂካዊ ምርቶች ለማሳደግ እቅድ መያዟን አመልክተዋል።

ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ለማጎልበት እየተከናወነ ያለው ስራ በጥሩ መንገድ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጣልያን ግዙፍ የኢንቨስትመንት እቅድ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ነው የገለጹት ኮሚሽነሩ።

ጣልያን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማልማት እና የጣልያንም ኩባንያዎች በግላቸው እና ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች በሽርክና መስራት የሚችሉባቸውን እድሎች ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ማህበረሰብ ተኮር የቤት ግንባታን ጨምሮ ሌሎች ኢኒሼቲቮች ላይ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው፥ ይህም በኢንቨስትመንት ሽርክና ለመስራት ያለውን እድል የሚያመላክት እንደሆነ ገልጸዋል።

የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ የሚያስችሉ እድሎች ከፊታችን አሉ ያሉት ኮሚሽነሩ አቅምን ወደ ሚታይ ውጤት ለመቀየር በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም