ብቁና ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ብቁና ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ባሕርዳር፤ ሕዳር 8/2018(ኢዜአ)፡- በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ የሚወክሉ ብቁና ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሽዊት ሻንካ ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማሕበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የባሕር ዳር ስታዲየምን እየጎበኙ ነው።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሽዊት ሻንካ እንደተናገሩት፤ ለስፖርት ዘርፍ እድገት በትኩረት እየተሰራ ነው።
ይህም እግር ኳስን ጨምሮ በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፍ መድረክ ብቁ ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእነዚህም ደረጃቸውን ጠብቀው እየተከናወኑ ያሉ ታላላቅ፣ መካከለኛና አነስተኛ ስታድየሞች ግንባታን ጠቅሰዋል።
ይህም ታዳጊና ህፃናትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ጠቁመው፤ ተግባሩ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማሕበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሀገሪቱ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ህፃናትና ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።
በሁሉም አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ ስታድየሞች ደረጃቸው ከፍ ያለና የሀገሪቱን የስፖርት ዘርፍ እድገት ለማላቅ የሚያግዙ እንደሆኑም ገልጸዋል።
የዛሬው ምልከታም ለተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ የዘርፉን ሪፖርቶች ትክክለኛነት ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ እርዚቅ ኢሣ ፤ የባሕርዳር ስታድየም የፊፉን እና ካፍን መስፈርቶች ማሟላት በሚችል አግባብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ስታዲዮሙ እግር ኳስን ጨምሮ ሌሎች 23 የስፖርት ዓይነቶችን ማስተናገድ እንዲችል ሆኖ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የስታድየሙ አብዛኛው ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑንና ቀሪዎቹን ፈጥኖ ለመፈፀም ርብርብ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማሕበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከስታዲየሙ በተጨማሪ የዕደ ጥበብ ማዕከላት፤ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንደሚጎበኙ ይጠበቃል፡፡