ቀጥታ፡

የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ 

ጋምቤላ ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለፁ። 

በዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝና ጥበቃ ዙሪያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አካሂዷል። 

ርዕሰ መስተዳድሯ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በክልሉ የዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥበቃና አከባበር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። 


 

በክልሉ የታራሚዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝና በማረሚያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሻሻል ረገድ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።  

በተለይም ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት የሚሆኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከልም ሌላው በትኩረት እየተሰራባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በቀጣይም በክልሉ በዜጎች ላይ ሊፈፀሙ የሚችሉ የመብት ጥሰቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳደሯ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት እንደ ሀገር የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ከመጣሳቸው በፊት አስቀድሞ የመከላከል ተግባር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል። 


 

የመብት ጥሰቶች ተፈጽመው ሲገኙም ተገቢውን እርምት እንዲያገኙ ከክልሎች ጋር የመስራት ባህል እየዳበረ እንዲሄድ ጭምር ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል። 

በጋምቤላ ክልል በማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝና መሠረተ ልማቶችን የማጠናከር ስራም መሻሻል ማሳየታቸውን ገልጸው፤ ለወደፊቱም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክተዋል። 


 

በሰብአዊ መብት ጥበቃ ዙሪያ የማህበረሰብ ግንዛቤ በማሳደግ ዜጎች በአቅራቢያቸው የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረጉ ስራም መጠናከር እንዳለበት ዋና ኮሚሽነሩ አመላክተዋል። 

በውይይት መድረኩ ላይ በክልሉ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም