ኤክስፖው ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችል ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ የተገኘበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኤክስፖው ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችል ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ የተገኘበት ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-አራተኛው ዓለም አቀፍ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ የማዕድን ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል አለም ዓቀፍ ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር) ገለጹ።
በማዕድን ዘርፍ ያለውን እምቅ ሀብት ወደ ብልፅግና ለመቀየር መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
በማዕድን ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከህዳር 4 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው አራተኛው ዓለም አቀፍ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ(MINTEX Ethiopia 2025) በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና እና የመዝጊያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በማዕድን ዘርፍ ያለውን እምቅ ሀብት ወደ ብልፅግና ለመቀየር መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው።
የኢትዮጵያ ማዕድን ዘርፍ እድገት እያሳየ መሆኑን አንስተው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዘርፉ ያሉ ችግሮች ተለይተው ማሻሻያ እንደተደረገባቸው ገልፀዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ለማዕድን የተሰጠው ትኩረት በዘርፉ ለውጥ ማስመዝገቡን ገልጸው፤ ይህን ተከትሎ ሀብት የማስተዋወቅ፣ የአሰራር ስርዓትና የፕሮጀክት አስተዳደርን ማሻሻል መቻሉን ተናግረዋል።
ኤክስፖው ከተለያዩ ዓለማት የተሰባሰቡ ባለሙያዎች፣የኢንዱስትሪው ተዋናዮችና ምሁራን የተገኙበትና የተለያዩ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሚያስችሉ ልምዶች የተወሰዱበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በኤክስፖው የተሳተፉ የዘርፉ አምራቾች በበኩላቸው ኤክስፖው ምርታቸውን ለማስተዋወቅና ልምድ ለመለዋወጥ እገዛ እንዳደረገላቸው አስረድተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በማዕድን ፍለጋና ማዕድን ማውጣት ዘርፍ የተሰማራው የኩርሙክ ጎልድ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ መርዕድ አማረ እንዳሉት፥ ኤክስፖው በዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማግኘት እድል ፈጥሮላቸዋል።
ኤክስፖው በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ከመንግስትና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመፍታት ውጤታማ መሆን የሚቻልበትን ልምድ ያጋራንበት ነው ብለዋል።
ላለፉት ስምንት አመታት ማዕድንን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው የቃል ፒኤልሲ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ቃልአብ አሰገደች በበኩላቸው፥ ኤክስፖው ዘርፉ የበለጠ እንዲነቃቃ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ኤክስፖው ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ልምድ ለመለዋወጥ እንዳገዛቸው ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ ለኤክስፖው መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።
የቀድሞ የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።