ቀጥታ፡

የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው

ድሬደዋ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን  የአስተዳደሩ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

በከተማው እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትም የተሽከርካሪ ፍሰቱን በማሳለጥ አደጋን ለመቀነስ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑም ተመላክቷል ።

 የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ አደጋ ቁጥጥር ዳይሬክተር ዋና ኢንስፔክተር ሰአዳ መሐመድ  ለኢዜአ እንዳሉት፤  የተሽከርካሪ አደጋን  በተቀናጀ መንገድ የመከላከል ስራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።


 

በአስተዳደሩ የአደጋ መንስኤዎችና የመከሰቻ ስፍራዎችን በጥናት በመለየት በተከናወኑ የመከላከል ስራዎች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶች፣ በክበባት፣ በገበያ ስፍራዎች፣ በታክሲ ፌርማታ፣ በሀይማኖት ተቋማት ስለ አደጋው አስከፊ ገፅታና የመከላከያ መንገዶች በስፋት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አንስተዋል ።

በተጨማሪም በተደጋጋሚ አደጋ በሚደርስባቸው አካባቢዎች የተለየ ስምሪት በማካሄድ፣ ለአደጋው ዋንኛ መንስኤ በሆነው የአሽከርካሪዎች ስነምግባር ላይ ንቃተ ትምህርት የመስጠትና ደንብ የሚተላለፉትንም የመቅጣት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት የአደጋ ፣ የሞትና የጉዳት መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ለአብነት በዘንድሮው የመጀመሪያ ሩብ በጀት አመት አምስት አደጋዎች ተከስተው አምስት ሰዎች ሲሞቱ  በ13 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት ማጋጠሙን ጠቅሰው፤ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት የአደጋ መጠን በስምንት፣ የሞት መጠንም በተመሳሳይ መልኩ በስምንት እንዲሁም የአካል ጉዳት በ19 መቀነሱን አመልክተዋል ።

ዋና ኢንስፔክተሯ አክለውም በአስተዳደሩ በከፍተኛ ደረጃ ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ አካባቢዎችና የትራፊክ መጨናነቅ የሚስተዋልባቸው ሰዓቶችን በመለየት ልዩ ግብረ ሃይል በማቋቋም የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነትና መድን ፈንድ ዳይሬክተር ኢንጂነር ሁሴን ጀማል በበኩላቸው፤ በከተማው እየተገነባ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የተሽከርካሪ ፍሰቱን በማሳለጥ አደጋ በመቀነስ ረገድ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኮሪደር ልማቱ ተጨማሪ አዳዲስ የተሸከርካሪና ምቹ የእግረኛ መንገዶች መፍጠሩ የተሽከርካሪ ፍሰቱን የሚያሳልጥና አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ነው ሲሉም አክለዋል።

የኮሪደር ልማቱ ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በተናበበና በተቀናጀ መንገድ በመስራት የተገኘውን ለውጥ ለማሳደግ ማስቻሉን ተናግረዋል ።


 

የኮሪደር ልማቱ የተሽከርካሪ አደጋን ለመከላከል የሚያግዙ መንገዶችን ወደ ስራ በማስገባቱ ሰላማዊ የተሽከርካሪ  ፍሰት እየተፈጠረ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የታክሲ አሽከርካሪ ወጣት የሽኩር አህመድ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም