የፖሊስ ተቋምን በማዘመን የሰላምና ልማት ሥራዎችን ለማጠናከር ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊስ ተቋምን በማዘመን የሰላምና ልማት ሥራዎችን ለማጠናከር ይሰራል
ሆሳዕና፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖሊስ ተቋምን ከወቅቱ ጋር በማዘመን የሰላምና ልማት ሥራዎችን ለማጠናከር ይሰራል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።
በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን "ከጂኦስትራቴጂያዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና" በሚል መሪ ሀሳብ ለፖሊስ አመራሮችና አባላት ያዘጋጀው ስልጠና በሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ ነው፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት፤ ፖሊስ ጸጥታና ደህንነትን በማስጠበቅ የክልሉ ሰላምና ልማት እንዲጠናከር አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
ፖሊስ ከማህበረሰቡ ጋር የቅርብ ቁርኝት ያለው መሆኑን አስታውሰው ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባና በየአካባቢው ልማት እንዲፋጠን ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ በማፋጠን የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምና ደህንነት አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ፖሊስ ይህን ሀላፊነቱን በላቅ ብቃት እንዲወጣ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለዚህም አሰራሩን ወቅቱን በሚመጥን መልኩ የማዘመን ሥራ እንደሚሰራና የፖሊስ አባላትን አቅም በተለያየ መንገድ የመገንባት ሥራም ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።