በሐረሪ ክልል የኮሪደር ልማት ስራ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የኮሪደር ልማት ስራ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ተጠናክሮ ይቀጥላል
ሐረር ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በሐረሪ ክልል የኮሪደር ልማት ሥራው በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በክልሉ በኮሪደር ልማት ስራዎች በተመዘገበው ውጤት አሻራቸውን ላኖሩ ተቋማት እና ማህበራት የእውቅና ሽልማት አበርክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በእውቅናው ስነ ስርዓት ላይ እንዳሉት በክልሉ የአመራር አንድነት፣ ውህደት፣ ቁርጠኝነትና የህዝብ ተሳትፎን በማጠናከር በኮሪደር ልማት ዘርፉ የተከናወነው ስራ ውጤት አስገኝቷል።
ከነዚህም መካከል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተሰጠው እውቅና አደጋ ተጋርጦበት የነበረውን የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን የኮሪደር ልማት ስራዎች እንደ አዲስ ታድጎታል ብለዋል።
የጀጎል ቅርስ ዙርያ እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በመልሶ ማልማትና ማስዋብ የተከናወነው ስራ ሁሉንም ያሳተፈ ውብ ማራኪና ለጎብኚ እርካታ እየሰጠ የሚገኝ መሆኑ ጠቁመው በዘርፉም ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የስራ ባህልንም ቀይሯል ብለዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩትን የኮሪደር ልማት ስራ ተቀብሎ በመተግበር ክልሉን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በክልሉ በኮሪደርና በሌሎች ተያያዥ የልማት ፕሮጀክቶች ምክንያት ከይዞታቸውና አካባቢያቸው ለተነሱ ባለይዞታዎች ተገቢ ካሳና ምትክ ቦታ በመስጠት የህብረተሰቡን ቅሬታ ከማስቀረት ባለፈ መላው የክልሉ ህዝብ ስራው ላይ በባለቤትነት ስሜት በስፋትና በንቃት ማሳተፍ መቻሉን ተናግረዋል።
የዛሬው መርሃ ግብርም በኮሪደር ልማት ዘርፍ ያስመዘገብነውን ስኬቶች በጋራ ከማክበር ባለፈ ለዚህ ታላቅ ምዕራፍ እውን መሆን የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምስጋናና እውቅና የሚሰጥበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በዚህም በሙሉ ፍቃደኝነት ይዞታውን፣ ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና እውቀቱን የሰጠው መላው የክልሉ ህዝብ ምስጋናና እውቅና ይገባዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሌሎች አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለድርሻ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በኮሪደር ልማት የተገኘው ዘርፈ ብዙ ውጤት ጅምርና ለቀጣይ ስራዎች የሚያነሳሳ እንጂ የሚያኩራራ አለመሆኑንም አቶ ኦርዲን አስገንዝበዋል።
በመድረኩም በኮሪደር ልማት ስራው ተሳትፎ አሻራቸውን ያበረከቱ ተቋማትና ማህበራት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እጅ ምስጋናና እውቅና ተቀብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።