ቀጥታ፡

በዓሉ ብዝሃነትን ለማስረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አሶሳ፤ ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ብዝሃነትን ለማስረጽ እና አንድነትን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ ገለጹ፡፡

አፈ ጉባኤዋ በሰጡት መግለጫ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አስታውቀዋል።

በዓሉ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በጥያቄና መልስ እንዲሁም ብዝሃነትን በሚያንፀባርቁ ሁነቶች እንደሚከበር  ጠቁመዋል።

በዓሉ በክልሉ ደረጃ በካማሽ ዞን ካማሽ ከተማ እንደሚከበር የገለፁት አፈ ጉባኤዋ፤ በበዓሉ ላይ ከክልሉ በተጨማሪ የአጎራባች ክልሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ብለዋል።

የካማሽ ዞን ከነበረበት የፀጥታ ችግር ተላቆ በተለያዩ የልማት ስራዎች አመርቂ ውጤቶችን እያሳየ በመሆኑ በዓሉ የዞኑን አሁናዊ ሁኔታ ለሌሎች አካባቢዎች ለማሳየት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የካማሽ ዞን በዓሉን ለማስተናገድ እና እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት መጀመሩንም አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል።

የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት በማጠናከርና ሀገራዊ ትርክት ለመገንባት የሚያግዝ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም