በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእጩ ምዝገባ ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእጩ ምዝገባ ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእጩ ምዝገባ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የግል ዕጩዎች ምዝገባ የሚጀመርበት ጊዜ በቀጣይ ይፋ እንደሚሆንም ጠቁሟል።
ምርጫ ቦርድ በጠቅላላ ምርጫ ለሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባደረገው ጥሪ እጩዎቻቸውን ቦርዱ በገለጸው ሲስተም ተጠቅመው እንደሚያስመዘግቡ ጥሪ አቅርቧል።
ምዝገባውን ለማከናወን የሚያስችሉ አስፈላጊ መረጃዎችን በማሟላት ከህዳር 8 እስከ ህዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት እና ከዚህ ቀደም ፓርቲው ለቦርዱ ባሳወቀው/ባሳወቃት ወኪል አማካኝነት በአካል በመገኘት ሠነዱን እንዲያቀርቡ አሳስቧል።
ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቅጾቹን ከ https://nebe.org.et/en/node/725 ላይ ማግኘት እንደሚችሉም ጠቁሟል።
በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለውድድር የተጠቀሙባቸው መወዳደሪያ ምልክቶችን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጠቀም ቀዳሚ መብት እንዳላቸው ቦርዱ ገልጿል።
ፖለቲካ ፓርቲዎች የሕጉን መሥፈርት የተከተለ የራሳቸውን የመወዳደሪያ ምልክት ማቅረብ እንደሚችሉና በአማራጭነት ቦርዱ ጋር በአካል በመቅረብ ቦርዱ ከሚያቀርበው የመወዳደሪያ ምልክት ዝርዝር ውስጥ መምረጥ እንደሚችሉም አመልክቷል።
የግል ዕጩዎች ምዝገባ ቦርዱ በገለጸው መተግበሪያ እንደሚያከናውንና የሚጀመርበትን ጊዜ በተመለከተ ቦርዱ በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።