ቀጥታ፡

ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዳማ ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡- ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ  የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻልና አሰራሮችን የመዘርጋት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።

ምክር ቤቱ በበይነ መንግስታት የፊስካል ግንኙነት ላይ ያተኮረ ውይይት ከፌዴራልና ክልሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር በአዳማ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

በውይይት መድረኩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር  እንዳመለከቱት፤  ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እውን እንዲሆን ምክር ቤቱ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻልና አሰራሮችን የመዘርጋት ስራ እያከናወነ ነው።

በተለይ የፌዴራል እና የክልሎች የጋራ ገቢ አስተዳደርና  ክፍፍል ቀመር፣ ጥቅል ድጎማና ውስን ዓላማ ያላቸው የበጀት ህጎች፣ አዋጆች እና ደንቦች በማሻሻልና አሰራሮች እየተዘረጉ ነው ብለዋል።


 

በተደረገው የአሰራርና የህግ ማዕቀፎች ማሻሻያም የጋራ ገቢ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰው፤  በዚህም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የሕዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን የሚያስችል ቁልፍ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል ።

ባለፉት ተከታታይ አምስት ዓመታት በጋራ ገቢ ክፍፍል፣ ጥቅል ድጎማና ውስን ዓላማ ባላቸው የበጀት ክፍፍል ላይ ሕዝቡ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በምክር ቤቱ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቱ ፀሐፊ አቶ ሃይሉ ኢፋ በበኩላቸው፤  ምክር ቤቱ  ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ለማረጋገጥ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል።


 

ለክልሎችና ለፌዴራል የሚሰጠው ድጎማ በተለይ የጋራ ገቢ ክፍፍል፣ ውስን ዓላማ ያላቸውና ጥቅል የድጎማ በጀቶች ውጤታማና በተጨባጭ ለሕዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ጥቅም ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም