የልማት ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ የፖሊስ አባላት ሚና ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ የፖሊስ አባላት ሚና ሊጠናከር ይገባል
ቦንጋ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-የተወጠኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የልማት ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ የፖሊስ አባላት ያለባቸውን ኃላፊነትና ሚና ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ።
"ከጂኦ ስትራቴጂካዊ ኩስመና ወይ ታደሰ ቁመና" በሚል መሪ ሃሳብ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከዞን፣ ከወረዳ እና ከከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ የፖሊስ አመራሮችና አባላት የተዘጋጀ ስልጠና በቦንጋ ከተማ መሰጠት ተጀምሯል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ እንደገለፁት፣ ከለውጡ ወዲህ በርካታ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ ተችሏል።
ለውጡ ብዙ መስዋእትነት የተከፈለበት መሆኑን ጠቅሰው የፖሊስ አባላቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲሁም ጀግንነት የሚጠይቁ ተግባራት ከፊታቸው እንዳሉ ሊገነዘቡ እንደሚገባም አንስተዋል።
ስለሆነም በመንግስት የተወጠኑ የልማት ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ የፖሊስ አባላት ኃላፊነትና ሚና ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የፖሊስ አባሉ አሁን ያለውን ክልላዊ፣ ሀገር አቀፋዊና ቀጠናዊ ሁኔታዎችን በተገቢው ለማወቅና ለመረዳት የሚያስችለው ስልጠና መሆኑን አፈ-ጉባኤው አስረድተዋል።
የክልሉ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ዓለሙ፤ ስልጠናው የዓለም-አቀፉን የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታ በመገንዘብ ተገቢውን ቁመና ለመያዝና የፖሊስ ሠራዊቱን አረዳድ የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
ስልጠናው ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥም ታውቋል።