ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን 117 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በኩታ ገጠም እየለማ ነው

አዶላ ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን 117 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደስታ ገብረየሱስ፤ በዞኑ የበጋ መስኖ ልማት በአዳዲስ የግብርና አሰራር በመታገዝ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በመስኖ ልማቱ እየተሳተፉ ለሚገኙ አርሶ አደሮች በግብርና ባለሙያ ድጋፍና ክትትል የሚደረግላቸው መሆኑን ጠቅሰው  የግብዓት አቅርቦትና የማሳ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።

በዚህም አርሶ አደሮቹ የመስኖ ስንዴን በመስመር፣ በኩታገጠምና በትራክተር በመታገዝ ለማልማት ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

እየለማ ከሚገኘው 117 ሺህ ሄክታር መሬት ላይም ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።

እስካሁንም ከ72 ሺህ 220 ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡


 

ለመስኖ ልማቱ ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና የስንዴ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮቹ መሰራጨቱን ገልጸው በልማቱ ስራ ላይ ከ213 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች መሳተፋቸውን አንስተዋል።

በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለመስኖ ልማቱ የተዘጋጀው መሬት ካለፈው ዓመት በ17 ሺህ 368 ሄክታር እንደሚበልጥ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የከርሰ ምድር ውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ ድጋፍና በልማት ጣቢያ ሰራተኞች ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ ደስታ ተናግረዋል።

በጉጂ ዞን በበጋ ስንዴ ልማት ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል የአዶላ ወረዳ የቂልጡ ሶርሳ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ታደሰ ረጋሳ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በበጋ መስኖ ልማት ከምግብ ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆኑን ያስታውሳል፡፡


 

ዘንድሮም ከልማት ጣቢያ ሰራተኞች ምክር በመቀበል የተሻለ ምርት ለማግኘት የማሳ ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መግባቱን ገልጿል፡፡

የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ምስጋናው ካሳዬ በበኩሉ፤ በመስኖ ልማቱ የሶስት ዓመታት ልምድና ተሞክሮ እንዳለው ተናግሯል፡፡


 

በቀረበላቸው ግብዓት በኩታገጠምና በመስመር የአስተራረስ ዘዴ ስንዴን በመስኖ በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራን ነው ብሏል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም