ቀጥታ፡

የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኙ የግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ በሚችሉ የግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን  የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የጋዜጠኞች  ቡድን በጉራጌ ዞን በግል ባለሀብቶች የለሙ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በዘርፉ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር በግብርና መስክ የሚፈሰውን መዋዕለ ንዋይ ለማሳደግ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ እንደሚገኝ የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መመሪያ አስታውቋል።  


 

የመምሪያው ሃላፊ ወይዘሮ አመተረኡፍ ሁሴን እንደገለጹት፤ በዞኑ በግብርናው ዘርፍ በግል ባለሃብቶች በ155 የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች 11 ሺህ 900  ሄክታር በላይ መሬት እየለማ ይገኛል። 

በግል ባለሃብቶች የሚከናወኑት የግብርና ስራዎች ለበርካታ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል ። 

ባለሃብቶቹ ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን በማስተዋወቅና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ እንደሚገኙም ገልጸዋል ።  

እንዲሁም ተኪ ምርት እና የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉ የግብርና ውጤቶች ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የዳኘ የተቀናጀ የእርሻ ልማት ባለቤት አቶ ዳኘ ዳባ፤ በዞኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መኖሩን አንስተው ሀገሪቱ ያላትን ሀብትና  የመልማት አቅም አቀናጅቶ መጠቀም ከተቻለ ልመናን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ይቻላል ነው ያሉት። 


 

ሰፊ ሀብታችንን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም ያሉት አቶ ዳኘ ለዘላቂ ዕደገት የስራ ባህላችንን መሰረታዊ በሆነ መልኩ መቀየር አለብን ብለዋል። 

የእርሻ ልማቱ በአሁኑ ወቅት በ 2 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ በርበሬ ፣ ሎሚ ፣ብርቱካን እና ሌሎችን የሰብል አይነቶች በማምረት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የበላይነህ ክንዴ እርሻ ልማት ዘርፋ ስራ አስፈጻሚ አንተነህ አባዋ (ዶ/ር) በግብርና ስራዎቻቸው ለውጭ ገበያ በሚቀርቡና  ለሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪዎች ግብዓት በሚሆኑ ምርቶች ላይ በስፋት  እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡ 


 

የኖርመና የተቀናጀ የእርሻ ልማት ድርጅት በ2 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ  ሱፍ፣ አኩሪ አተር፣ ሩዝ፣ ቅመማ ቅመም እና ሌሎች የሰብል አይነቶችን በማምረት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

ድርጅቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ አዳዲስና ተፈላጊ የሰብል ዝርያዎችን በማስተዋወቅና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመፍጠር ለግብርናው ዘርፍ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም