ቀጥታ፡

የክልሉ ፖሊስ ሕግን በማስከበር ሚናውን እየተወጣ ነው

አሶሳ፤ ሕዳር 8/2018(ኢዜአ)፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ የሕብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት እያስጠበቀ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሚናውን እየተወጣ መሆኑን የክልሉ  ርዕሰ መስተዳድር  አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ "ከጂኦስትራቴጂያዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና" በሚል መሪ ሐሳብ ለክልሉ ፖሊስ እና ፀጥታ አካላት የሚሰጠውን ስልጠና አስጀምረዋል።


 

በዚህ ወቅት  ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንደተናገሩት፤ የፀጥታ አካላት ዋነኛው ተልዕኮ የሕብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅና ሕግ  ማስከበር ነው።

ተለዋዋጭ የሆነውን ወቅታዊ ጂኦፖለቲክስ በመረዳት እና በተደመረ አቅም የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ የሚያግዝ የፀጥታ ሀይል እንዲኖር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ከዚህ ባለፈ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሀገሪቷ የምታከናውናቸው ግዙፍ የልማት እንቅስቃሴዎች ደህንነት ማስጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሀሩን ዑመር በበኩላቸው፤ ስልጠናው በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የፖሊስ አባላት ተቀራራቢ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና ለላቀ ተልዕኮ ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለሁለት ቀናት በተሰናዳው ስልጠና ላይ  የክልሉ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም