ቀጥታ፡

የኩላሊት ዕጥበት ማዕከሉ ሕይወታችንን ታድጎልናል - ታካሚዎች   

ድሬዳዋ፤ ሕዳር 8/2018(ኢዜአ)፡-  በድሬዳዋ ሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል የተገነባው የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል  በሚሰጣቸው ሕክምና ሕይወታቸውን እየታደገው መሆኑን  ታካሚዎች ገለጹ። 

በሆስፒታሉ  የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ለ172 የኩላሊት ህሙማን ተገቢውን ሕክምና በመስጠት ሕይወት መታደጉን  የማዕከሉ አስተባባሪ አስታውቀዋል። 

የድሬዳዋ አስተዳደር ባለሃብቶችንና ግብር ሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር ማዕከሉን በማስገንባት  አገለግሎት መስጠት  ከጀመረ ሁለት ዓመታት እንደሆነው ተመልክቷል። 


 

በዚህ የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል በመታከም ላይ የሚገኙት ህሙማን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የማዕከሉ መገንባት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሕሙማንን ችግር በመፍታት ሕይወታቸውን እየታደገ ይገኛል።

ከተገልጋዮች መካከል ወይዘሮ ገነት አበበ በሰጡት አስተያየት፤ ማዕከሉ መገንባቱ የኩላሊት ዕጥበት የሚፈልጉ ህሙማን በቀላል ወጪ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።

ማዕከሉ በመኖሩ ኩላሊታችን እየታጠበ ለመተንፈስ እና ለመራመድ ችለናል ያሉት ወይዘሮ ገነት፤ ይህ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

አቶ ጀማል ረሺድ በበኩላቸው፤  የማዕከሉ መገንባት በቀላሉ እና በቅርበት ተገቢውን ሕክምናና ክትትል ለማድረግ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።


 

ላለፉት አስራ አንድ ወራት የሕክምና ባለሙያዎቹ ለኩላሊታቸው  ተገቢውን ሕክምናና እንክብካቤ እያደረጉላቸው በመሆኑ ጤናቸው መሻሻሉን ገልጸዋል ።

ታካሚዎቹ፤ የኩላሊት ዕጥበት ማዕከሉ እየሰጣቸው ባለው ሕክምናና በሚያደርግላቸው እንክብካቤ ሕይወታቸውን እየታደገ መሆኑን ተናግረዋል። 

የማዕከሉ አስተባባሪ ሲስተር ቅድስት ደሳለኝ በበኩላቸው፤  ማዕከሉ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በድሬዳዋ እና በተጎራባች ክልሎች በልዩ ልዩ ምክንያት ለኩላሊት ህመም ለተጋለጡ 172 ሰዎች ህክምና በመስጠት ህይወት መታደጉን አስታውቀዋል። 


 

ማዕከሉ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሕሙማን በአነስተኛ ወጪ ሕክምና በመስጠት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ማዕከሉ የሪፈራል ቅብብሎሽን እና የሕክምና ባለሙያዎችን ጊዜና እንግልት በማስቀረት ወሳኝ ሚና መጫወቱንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም