የኢትዮጵያን ብቃት እና ዐቅም በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዐይቻለሁ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብቃት እና ዐቅም በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዐይቻለሁ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበበ፤ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን የማድረግ ብቃት እና ዐቅም በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዐይቻለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ ቤቱን ቀድሞ ከነበረበት ቀይሮ ወደ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ሕንፃ በተዛወረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም፥ በአጠቃላይ ዛሬ ያየሁት ነገር ሰው የጠራ ራዕይ ካለው፣በከፍተኛ ዲሲፕሊን የሚሠራ ከሆነ አንድን ነገር ባየው ልክ ማሳካት እንደሚችል ነው ብለዋል።
ሁሉ ነገር እየተከናወነ ያለው በኢትዮጵያውን በመሆኑ ኢትዮጵያ የማድረግ ብቃት ያላት ሀገር እንደሆነች ዐይቻለሁ ብለዋል።
ያሉን ሕንጻዎችና ስፍራዎች ይሁነን ብለን አስበን ብንሠራቸው እጅግ ያማሩ መሆን እንደሚችሉም ተመልክቻለሁ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በተቋም ደረጃ ካስጀመርነው አምስት ዓመት ገደማ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ የተቋም ግንባታ ሥራው እጅግ አስደማሚ መሆኑን ተናግረዋል።
ራዕይ እና ዲሲፕሊን ሲገናኙ ምን ዓይነት ነገር መፍጠር እንደሚቻል ይህ ተቋም ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመሥሪያ ቦታ ብቻ እንኳን ቢወሰድ ለኢትዮጵያ ዐይን ገላጭ፣ አዲስ ምልከታ፣ አዲስ ዕይታን የሚገልጥና የሚያሳይ በጣም ለሥራ የተመቸ ወጣቶች ረዥም ሠዓት ሊሠሩ የሚችሉበት ተቋምና ሥፍራ ሆኗል ሲሉም ገልጸዋል።
የዛሬ አምስት ዓመት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚለውን ሐሳብ ስናነሳ ተቋም ይፈጠር ሲባል በእኛም ውስጥ ብዙዎች በቀላሉ የገዙት ሐሳብ አልነበረም ሲሉም አውስተዋል።
ነገር ግን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጅ የሚያስብበትን መንገድ፣ኢማጅን የሚያደርግበትን መንገድ፣ ፖሲብሊቲን የሚያይበትን መንገድ እየቀረጸ መጥቷል ሲሉም አብራርተዋል።