ቀጥታ፡

የፌዴራል መንግስት ወደ ቀያችን እንድንመለስ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም የቀድሞው ህወኃት እንቅፋት ሆኖብናል

ሽረ እንዳስላሴ፤ህዳር 8/2018(ኢዜአ)፦የፌዴራል መንግስት ወደ ቀያችን እንድንመለስ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም የቀድሞው ህወኃት እንቅፋት ሆኖብናል ሲሉ የሽረ እንዳስላሴ ተፈናቃዮች ተናገሩ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ቀደም ብለው ማብራሪያ የሰጡት የትግራይ ክልል የቀድሞ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በክልሉ መጠቀሚያ እያደረጉ ያሉ አካላት መኖራቸውን መግለፃቸው ይታወሳል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሳይመለሱ በየመጠለያዎቹ ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑንና የዚህ ችግር ምክንያቱ የቀድሞ ህወሓት አመራሮች መሆናቸውን የኢዜአ ሪፖርተር በሽረ እንዳስላሴ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ገልፀዋል።

የፌዴራል መንግስት ተፈናቃዮች ወደ ቀያችን እንድንመለስ በተደጋጋሚ ቢገልፅም የቀድሞው ህወኃት አመራሮች እንቅፋት በመሆናቸው እስካሁን ሊሳካ አልቻለም ሲሉ አንስተዋል።

ተፈናቃዮቹ ለዓመታት በመጠለያ ውስጥ ለችግርና እንግልት እየተዳረግን ቀጥለናል በማለት በምሬት ተናግረዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት ከአምስት ልጆቻቸው ጋር ከወልቃይት ተፈናቅለው በሽረ እንዳስላሰ ከተማ "አዲ ከንቲባይ" በትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙት አቶ አንበሳ በርሄ፣ የመመለስ ተስፋ ይዘን ለአመታት ብንጠባበቅም ተግባራዊ ምላሽ አጥተናል ብለዋል።


 

በዚህ ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግስት የፀና አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን ብናውቅም የመመለሱ ጉዳይ በቀድሞው ህወሓት አመራሮች ምክንያት ፈተና ሆኖብናል ብለዋል።

በመሆኑም ካለንበት እንግልትና ስቃይ ወጥተን ወደ ቀያችን እንድንመለስ የመንግስትን እገዛና ድጋፍ አሁንም እንሻለን ብለዋል።

ሌላኛዋ ተፈናቃይ ወ/ሮ ልእልቲ፣ ለአምስት አመታት ከቤት ወጥቶ በመጠለያ መኖር ምን ያክል ከባድና ዋጋ ያስከፈላቸው መሆኑን አንስተው፣ከእንግዲህ ይብቃን መልሱን ሲሉ ተማፅነዋል።


 

በዚሁ መጠለያ ያገኘናቸው አቶ ኃብቶም ገ/ክርስቶስ፣ በመጠለያ ለዓመታት የደረሰብን እንግልትና ስቃይ ይብቃን መፍትሄ እንሻለን በማለት ተማፅነዋል።

ሁላችንም ወደ ቀያችን እንድንመለስ በፌዴራል መንግስት የሚቀርበው ተደጋጋሚ ጥሪ ተቀባይነት ማግኘት አለበት ያሉት ተፈናቀዮቹ በመጠለያ የዓመታት የስቃይ ህይወት ይብቃን ወደቀያችን እንመለስ በማለት ጠይቀዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የትግራይ ክልል ህዝብ ሰላምና ልማት ይሻል፣ ተፈናቃዮችም ከምንም በፊት ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም