ቀጥታ፡

ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ወደ ክልሉ የሚመጡ እንግዶች የተለያዩ መስኅቦችን ይጎበኛሉ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 8/2018 (ኢዜአ)፡- ለ20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አከባበር ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለሚመጡ እንግዶች የቱሪዝም መስኅቦችን ለማስጎብኘት ዝግጅት ተደርጓል።


 

ቀኑ በክልሉ መከበሩ ተፈሯዊ፤ ታሪካዊና ባህላዊ የቱሪዝም መስኅቦች ለማስተዋወቅ እንደሚጠቅም የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ መሐመድኑሪ ሳልያ ተናግረዋል።


 

በዚህም መሠረት እንግዶች ሲመጡ በቀላሉ እንዲጎበኟቸው ዋና ዋና የቱሪዝም መስኅቦች ተለይተው በቂ ዝግጅት መደረጉን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።

የተለዩት መዳረሻዎችም፤ ጥያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ፣ ምድረ ከብድ አቦ ገዳም፣ የስልጤ ሙዚየም፣ ሀረ ሸይጣን ሐይቅ፣ አርቶ ፍል ውኃ፣ ሴራ ፌስቲቫል፣ መጨፈራ ሐይቅ፣ ወገና የከብቶች ቆጠራ ሥርዓት፣ ሃምበርቾ 777 ኢኮ ቱሪዝም እና ሶዲቾ ዋሻ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

እንዲሁም አጆራ ፏፏቴ፣ ጀፎር፣ ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ፣ ብርብርሳ ፏፏቴ፣ ጥቅምት 17 ባህላዊ የመድኃት ለቀማ የሚከናወንበት ስፍራ (ሳሞ ኤታ)፣ኦሞ ሰው ሠራሸ ሐይቅ፣ መሪሾ ፌስቲቫል፣ ዘቢሞላ ሀድራ፣ ደቀንሽ ሞላ ፏፏቴ፣ ራጋ ማጋ የግጭት አፈታት ሥርዓት እና ፋቃ ከንፈልቻ ዋሻ በእንግዶች እንዲጎበኙ የተለዩ መስኅቦች መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም የባህል ምግቦችና አለባበስን እንግዶች በሚያልፉበትና በሚያርፉበት ለማስተዋወቅ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ሆቴሎችና የእንግዳ ማረፊያዎችን ጨምሮ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በክልሉ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን አቶ መሐመድኑሪ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም