ቀጥታ፡

ጤናማ አመጋገብ ሲባል ምን ማለት ነው?

በፈረንጆቹ 2024 የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት እና የዓለም ጤና ድርጅት ባወጡት መመሪያ መሠረት ጤናማ ምግብ አራት መሠረታዊ መርሆዎችን ይይዛል። እነሱም፤ በቂ መሆን፣ ሚዛንን መጠበቅ፣ ልከኝነት እና የተሰባጠረ መሆናቸውን የሥርዓተ-ምግብ፣ የአካባቢ ጤናና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተመራማሪ ዳዊት ዓለማየሁ ለኢዜአ ተናግረዋል። በዚህም መሠረት፡-

👉 በቂ መሆን፦ ሁሉንም አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችና እነሱን የያዙ የምግብ መደቦች በበቂ መጠን እንዲሁም ከፍላጎት በላይ ሳይሆን ማቅረብ ማለት ነው። በዚህም የአመጋገብ ፍላጎቶችን ከዕድሜ፣ ጾታ፣ የእንቅስቃሴ ደረጃ እና የፊዚዮሎጂ ሁኔታ ጋር ማመጣጠን አስፈላጊ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

👉 ሚዛንን መጠበቅ፡- ማክሮኒዩትሬንቶች (ፕሮቲን፣ ስብና ካርቦሃይድሬት) እድገት፣ ጉልበትና አጠቃላይ ጤናን በሚደግፍ መጠን መወሰድ አለባቸው ብለዋል።

👉 ልከኝነት፡- ከጤና አደጋዎች ጋር የተገናኙ ንጥረ ነገሮች እንደ ስኳር፣ ሶዲየም (ጨው)፣ የሳቹሬትድ ፋት (ጠጣር ስብ) እና ትራንስ ፋት (ተፈጥሯዊ ባሕርይው በፋብሪካ የተቀየረ ስብ) በተጠበቀ ገደብ ውስጥ መሆን አለበት ማለት ነው። ይህም ለህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

👉 ስብጥር፡- የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በተመጣጠነ ሁኔታ ማካተት በቂ ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት ከማስቻሉ በላይ የምግብ እጥረትን ለመከላከል ይረዳል ብለዋል።

የተሰባጠረ አመጋገብ ማለት በአንድ ገበታ በአንድ ጊዜ ቢያንስ አራት የምግብ ምድብ እንዲሁም በቀን ስድስት የተለያየ የምግብ ምድብ የያዘ ማለት ነው።

🫵 የኢትዮጵያ ምግብን-መሰረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ ስድስት የምግብ መደቦች መያዙን አብራርተዋል። በዚህም መሠረት፡-

1ኛ. እህልና ሥራሥር (እንጀራ፣ ዳቦ፣ ቆጮ እና ቆሎ)፣

2ኛ. ጥራጥሬ (አተር፣ ምስር፣ ሽምብራ እና ባቄላ)፣

3ኛ. ለውዝ እና የቅባት እህል (ለውዝ፣ ሰሊጥ፣ ኑግ፣ ሱፍ፣ ተልባ)፣

4ኛ. የእንስሣት ተዋፅዖ (የዶሮ፣ የከብት፣ የፍየል፣ የበግ ሥጋ እና ዓሣ፣ ዓይብ፣ እርጎ)፣

5ኛ. አትክልትና ፍራፍሬ (እንደ ወጥ ወይም ሰላጣ የሚዘጋጁ አትክልቶች፣ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ አቮካዶና ሌሎች ፍራፍሬዎች) እንዲሁም

6ኛ. ቅቤ እና ዘይት መሆናቸውን አብራርተዋል።

ጤናማ ምግብ ደኅንነነቱ የተጠበቀ መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ የኑሮ ሁኔታና ዐቅም በፈቀደ መጠን አመጋገብን ጤናማ በማድረግ ቀድሞ በበሽታ የመያዝ ዕድልን መቀነስ እንደሚቻል ባለሙያው መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም