ኢንስቲቲዩቱ በጤና፣ በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍ እያደረገ ያለው የመሪነት አስተዋፅኦውን እየተወጣ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲቲዩቱ በጤና፣ በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍ እያደረገ ያለው የመሪነት አስተዋፅኦውን እየተወጣ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦ ኢንስቲቲዩቱ በጤና፣ በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍ እያደረገ ያለው የመሪነት አስተዋፅኦውን እየተወጣ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
በክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ትላልቅ የመረጃ ቋቶች፣ የመረጃ ፍለጋ፣ ሮቦቲክስ እና ኢመርሲቭ ቴክኖሎጂዎች አቅሙን በማጎልበት ላይ ይገኛል ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ጽሕፈት ቤቱን ቀድሞ ከነበረበት በመለወጥ መሃል ከተማ ወደ ቀድሞው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሕንፃ አዛውሯል ብለዋል።
በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ አስደናቂ የግንባታ ለውጥ እና ዘመናዊ የመሥሪያ ሥፍራ ጥበብን በማሳየት ለሠራተኞቹ እጅግ ምቹ የሆነ ስፍራንም መፍጠር ችሏል ነው ያሉት።
ተቋሙ በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሕይወታችንን በፍጥነት በመቅረጽ ውስጥ ያለውን ስፍራ በሚያንፀባርቅ እና ሀገራችንም በዚህ አለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር በንቁነት መሳተፏን በሚያረጋግጥ መንገድ ከፍታ ላይ ደርሷል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በጤና፣ በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍ እያደረገ ያለው የመሪነት አስተዋፅኦውን እየተወጣ ሲሆን በክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ትላልቅ የመረጃ ቋቶች፣ የመረጃ ፍለጋ፣ ሮቦቲክስ እና ኢመርሲቭ ቴክኖሎጂዎች አቅሙን በማጎልበት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
በቅርቡ የተጀመረው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስታርት አፕ መዐከል ደግሞ ይኽንን ከባቢ የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል በመልዕክታቸው።
ዜጎች ሀሳብ ብቻ ይዘው በመምጣት ፕሮቶታይፕ ለመፍጠር፣ ለማባዛት ብሎም ከግሉ ዘርፍ ኢንቬስተሮች ጋር እንዲገናኙ እድል ያመቻቻል። እስከ አሁን 200 ሀሳብ ፈጣሪዎች በዚህ እድል ተጠቅመዋል ሲሉም አስታውቀዋል።