ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ማደጉ ኃላፊነቱን የበለጠ ለመወጣት ያስችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ማደጉ ኃላፊነቱን የበለጠ ለመወጣት ያስችለዋል
ደብር ማርቆስ ፤ ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ማደጉ በጥናትና ምርምር ታግዞ የተጣለበትን የህዝብና የመንግስት ሀላፊነት የበለጠ ለመወጣት አቅም የሚፈጥርለት መሆኑ ተመለከተ።
ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት እንዲያድግ አስተዋጽኦ ላደረጉና በተልዕኮ አፈጻጸም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የኮሌጁ አመራሮችና አባላት ዛሬ የማዕረግ እድገትና እውቅና ተሰጥቷል።
የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚኒሽነር አበበ ደለለ በወቅቱ እንደገለጹት፡ ኮሌጁ ከተቋቋመ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የፖሊስ አመራሮችና አባላትን በእውቅትና በክህሎት በማነጽ አፍርቷል።
በዚህም የፖሊስ አመራሮችና አባላትን በአካል ብቃት፣ በስነ ምግባር፣ በእውቀትና በስነ ልቦና በማነጽ በክልሉ ሰላምን ለማስፈንና ወንጀልን ለመከላከል አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ኮሌጁ ከሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ማደጉን ጠቁመው፣ ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉና በተልዕኮ አፈጻጸም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የኮሌጁ አመራሮችና አባላት የማዕረግ እድገትና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል ብለዋል።
ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ማደጉ በጥናትና ምርምር ላይ በማተኮር መንግስትና ህዝብ የጣሉበትን ሃላፊነት በተሻለ ለመወጣት ተነሳሽነትን ፈጥሯል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በበኩላቸው፤ ኮሌጁ የሰለጠነ የፖሊስ ሃይል በማፍራት ወንጀልን ለመከላከል በሚሰራው ሥራ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ማደጉ አሰራሩን በማዘመን የወንጀል መከላከል አቅሙን እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።
ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ማደጉ አሰራሩን በማሳደግ በቴክኖሎጂና ምርምር ላይ አተኩሮ እንዲሰራ ያስችለዋል ያሉት ደግሞ የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ ናቸው።
የማዕረግ እድገት ካገኙት መካከል ኮማንደር ታደለ ፈንቴ እንዳሉት የማዕረግ እድገቱ በቀጣይ በህብረተሰቡ ተሰትፎ ውጤታማ ሥራ ለመስራት የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።