ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ከ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር አብረው ይኖራሉ 

ሰመራ ፤ ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ከ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር አብረው እንደሚኖሩ የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ገለፀ።

በአገር አቀፍ ደረጃ 35ኛው የስኳር ሕመም ቀን "ስኳር ህመምና ደህንነት፣ በስራ ቦታ ስለ ስኳር ህመም ይበልጥ ይገንዘቡ፣ ተጨማሪም ድጋፍ ያድርጉ" በሚል መሪ ሐሳብ በሰመራ ከተማ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ እንዳሉት፤ ተላላፊ ካልሆኑና በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፉ ከመጡ ህመሞች አንዱና ዋነኛው የስኳር ህመም ነው።


 

የሕመሙን የመከላከያ መንገዶች በአግባቡ በመተግበር በሽታውን እስከ 80 በመቶ በመከላከል ማስቀረት እንደሚቻልም ተናግረዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር አብረው ይኖራሉ ያሉት ዶክተር ታረቀኝ፤ በዚህም በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 79 የሆኑ ሰዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በዓለም ላይም የህሙማን ቁጥር እየጨመረ የመጣው በማደግ ላይ ባሉና ባላደጉ አገራት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም ከ5 የስኳር ህመምተኛ 4ቱ የሚገኙት ባላደጉ አገራት መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበሩ ህመሙ የሚያስከትለውን ጠንቅ በመረዳት በተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች በስራ ቦታ በመገኘት ለሠራተኛው፣ ለአሰሪዎቹና ለቅርብ ረዳትና ኀላፊዎች ግንዛቤ የመፍጠርና የማሳደግ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።


 

ላለፉት ሁለት ሳምንታት የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የተሰሩ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ሁለት ሳምንትም ይህ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር 96 ቅርንጫፉች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው በአፋር ክልል ከሚገኙት አራቱ ቅርንጫፎች በተጨማሪ በአዋሽ ሰባት ከተማ ቅርንጫፍ  ለመክፈት መታቀዱንና የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥልም ነው ያስረዱት።

በአፋር ክልል ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር አቶ አህመድ ዓሊ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር፣ የአፋር ስኳር ህመም ማህበር እንዲጠናከርና እንዲደራጅ የላቀ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።


 

በተለይ መድሃኒቶች እንዲቀርቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ጠቅሰው በዱብቲ፣ አሳይኢታና መሐመድ አክሌ ሆስፒታሎች የተከናወኑትን ለአብነት አንስተዋል።

በዕለቱ የአፋር ክልል ስኳር ህመም ማህበር አባላት፣ የሆስፒታል ዳይሬክተሮችና የጤና ባለሙያዎች በተገኙበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል። የጤና ምርመራ፣ የእግር ጉዞና የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም