ቀጥታ፡

ከተሞች አረንጓዴ እና ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ከተሞች በከፍተኛ መነቃቃት ላይ ይገኛሉ

አዲስ አበባ፤ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦ከተሞች አረንጓዴ እና ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች በከፍተኛ መነቃቃት ላይ እንደሚገኙ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም "የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ሀሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡


 

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የፎረሙን ሁለተኛ ቀን ውሎ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም ፎረሙ ከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ በማንሰራራት ላይ ባሉበት ወቅት መከበሩ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።

በፎረሙ 143 ከተሞች መገኘታቸውን እና 7000 ኤግዚቢሽን አቅራቢዎች መታደማቸውን ገልጸዋል።

በፎረሙ የዘርፉን ተወዳዳሪነት እና ተግዳሮቶችን መቅረፍ የሚያስችሉ የፓናል ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

ከተሞች ከዚህ ቀደም የድህነት ማሳያ እንደነበሩ አስታውሰው፥ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ዛሬ ላይ ከተሞች የብልጽግና ማሳያ ሆነዋል ብለዋል።


 

በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ፍጥነት እና ጥራት የተከናወነው የኮሪደር ልማት ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን ማስገኘቱን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የኮሪደር ልማት በ73 ከተሞች መስፋታቸውን ገልጸው፥ ይህም መንግስት ለዜጎች የምትመች ሀገር የመገንባት ስራው ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኮሪደር ልማት ኢንዱስትሪዎች እንዲነቃቁ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ የስራ እድል መፍጠሩን እና የስራ ባህልንም በጉልህ የቀየረ መሆኑን አመላክተዋል።

እንዲሁም የከተሞች እንቅስቃሴን በማሳደግ ገቢያቸው እንዲያድግ ማስቻሉንም አንስተዋል።

የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ የተሻለ እንዲሆንም የኮሪደር ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።


 

የከተሞች ፕላን በአግባቡ መመራት ባለመቻሉ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የወጡ የአሰራር መምሪያዎች ቢኖሩም ተግባራዊ እንዳልነበሩ ገልጸው፥ ተግባራዊ መሆን የቻለው በለውጡ መንግስት መሆኑን ተናግረዋል።

ከተሞች አረንጓዴ ፣ ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከተሞች በከፍተኛ መነቃቃት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም