ቀጥታ፡

የባህላዊ ምህንድስና ማሳያ -ጀፎረ

የባህላዊ ምህንድስና ማሳያ እና የማህበራዊ መስተጋብር መከወኛ -ጀፎረ

የምህንድስና ጥበብ ባልነበረበት ዘመን የተመሰረተ የኢትዮጵያዊነት ልክና መልክ መገለጫ -የጀፎረ መንደር ፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ የሚገኘው ጀፎረ በሁለት መንደሮች መካከል የሚገኝ ሲሆን ትርጉሙም የጋራ መንገድ ማለት ነው።


 

በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው ይኖሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አደጋ በሚገጥማቸው ወቅት የጩኽት ድምፅ ቢያሰሙም የሚደርስላችው ሰው በቅርብ ስላልነበር ለደህንነታችው ሲሉ ተሰባስበው መንደሩን እንደመሰረቱት ይነገራል።

የጉራጌ ባህላዊ ጥበብ ማሳያ የሆነው ጀፎረ ለአካባቢው ማህበረሰብ ምቹና ዘመናዊ አኗኗርን ያላበሰና ለአካባቢው ነዋሪዎች  የጋራ መጠቀሚያ ነው።


 

የአካባቢው ነዋሪ ሀጂ ከማል አህመድ ጀፎረ ማህበራዊ መስተጋብር በተግባር የሚታይበት የአካባቢው ነዋሪዎች በመተጋገዝና በመደጋገፍ የሚኖሩበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።


 

ጀፎረ አረንጓዴነቱ እና ጽዳቱ የተጠበቀ ፣ዘመናዊ አኗኗር የሚታይበት የኮሪደር ልማት እሳቤ ማሳያም ነው፡፡ 

ጀፎረ በርካታ አገልግሎት የሚሰጥ፣ ብስራትና መርዶን የመሰሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚከወኑበት፣ አባቶች ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የሚሰጡበት የማህበረሰብ የወል ሀብት መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ከአባቶቻችን የተቀበልነውን ውብና ጽዱ የጀፎረ መንደር  ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደ አይን ብሌናችን እንጠብቀዋለን ያሉት ደግሞ ጨዋነሽ ተክሊ ናቸው።


 

በእንግዳ ተቀባይነቱ የሚታወቀው የጀፎረ ማህበረሰብ በአካባቢው ባህል መሰረት እርስ በእርስ በመረዳዳት ወንድማማችነት በተግባር የሚታይበት መሆኑንም አንስተዋል።


 

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው፤ የቀደምት አባቶች የቤት አሰራራቸውም ሆነ አሰፋፈራቸው የነገን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ጀፎረ የገጠሩ ማህበረሰብ የተሻለ ኑሮ እንዲኖረው በማለም ለተጀመረው የኮሪደር ልማት መነሻ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የባህላዊ ምህንድስና ውጤት የሆነው ጀፎረ ዘመናዊ የአኗኗር ጥበብን የያዘ መሆኑን ተከትሎ ያሉትን ጸጋዎች በማልማት አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም